ሚዲያው ‘ቡቤ’ የተሰኘ ሲትኮም ድራማ ወደ ተመልካች ሊያደርስ ነው
በዘመናዊው ዓለም የትልልቅ ከተሞች ህይወት ያለ ሚዲያና መዝናኛ ሊታሰብ አይችልም። ከተማ ማለት የሕንፃዎች ስብስብ ብቻ ሳትሆን የባህል፣ የንግድ፣ የፖለቲካና የፈጠራ ስራዎች መገናኛ ማዕከልም ናት። በዚህ መገናኛ ውስጥ ደግሞ የሜትሮፖሊታን ሚዲያ በመረጃ እና መዝናኛ ከመኖሪያ ቤታችን ይደርሳል።
የሜትሮፖሊታን ሚዲያ ማለትም ሬዲዮ፣ ቴሌቪዥን፣ ጋዜጦችና የዲጂታል ገጾች የከተማውን ነዋሪ ስሜትና ፍላጎት የሚያንፀባርቁ ናቸው። የመዝናኛ ፕሮግራሞች ደግሞ የሜትሮፖሊታን ዋነኛ ክፍሎች ናቸው።
አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክም የአዲስ አበባን ፈጣን የለውጥ ጉዞና የነዋሪውን ሁለንተናዊ ፍላጎት መሰረት በማድረግ፣ የሜትሮፖሊታን ሚዲያነቱን የሚመጥኑ ዘመናዊ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን በመቅረጽ ግንባር ቀደም ተዋናይ ሆኖ ብቅ ካለ ሰነባብቷል። ተቋሙ የከተማዋን ገጽታና የነዋሪዎቿን የአኗኗር ዘይቤ የሚያንፀባርቁ ልዩ ልዩ የጥበብ ስራዎችን ለተመልካች በማቅረብ፣ የአዲስ አበባን የባህል ማዕከልነት በይበልጥ እያደመቀ፣ የትውልድ ድምጽነቱን እያሳየና የሜትሮፖሊታን ሚዲያነቱን በተግባር እያሳየ ይገኛል። ይህ ጥረትም ሚዲያው ከመረጃ አቅራቢነት ባለፈ የከተማዋን ህዝብ የመዝናኛ ፍላጎት ከማሟላት አንጻር አይተኬ ሚና አለው፡፡ ለዚህ ደግሞ ከባለድርሻ አካላት ጋር ያለውን ቅንጅትና ትብብር አጠናክሮ ቀጥሏል። ከሰሞኑ “ቡቤ” የተሰኘ ሲትኮም ድራማ ለማስጀመር ከጃንኮ ፕሮዳክሽን ጋር ያደረው የሥራ ስምምነት ለዚህ አንዱ ማሳያ ነው፡፡
የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ካሳሁን ጎንፋ በፊርማ ስነ ስርዓቱ ላይ፣ “ተቋሙ የትውልዱን ፍላጎት የሚያሟሉ ይዘቶች ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ ነው፡፡ አሁን ላይ እያደገ የመጣውን የመዝናኛ ኢንዱስትሪ ፍላጎት ለማሟላት በኪነ-ጥበብ ዘርፍ ላይም ትኩረት አድርጎ እየሰራ ይገኛል” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ዋና ስራ አስፈጻሚው ሁለተኛውን ኤኤምኤን ፕላስ ቻናል ካቋቋምን በኋላ የህዝባችንን የሚዲያ ጥማት ደረጃ በደረጃ እያረካን ነው ሲሉም አስረድተዋል፡፡

አቶ ካሳሁን አዲስ አበባ ለኪነ-ጥበብ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት የቴአትር ቤቶችንና የኪነ-ጥበብ ማቅረቢያ አደባባዮችን እያሰፋች መሆኑን ጠቅሰው፣ ጥበባዊ ይዘቶችን ማምረት ደግሞ የአርቲስቶችና የሚዲያ ተቋማት ድርሻ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ከጃንኮ ፕሮዳክሽን ጋር የተደረገው ስምምነት የተመልካቾችን ፍላጎት የሚያሟላና የወጣቶችን ጥያቄ የሚመልስ በመሆኑ፣ የከተማነት ገጽታን የሚያንፀባርቁ ይዘቶችን ለተመልካች ለማድረስ ትልቅ ዕድል እንደሚፈጥር አንስተዋል፡፡
አቶ ካሳሁን አክለውም፣ “አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ በየጊዜው መሻሻል እያሳየ፣ አመርቂ ውጤትም እያመጣ የሚገኝ ሜትሮፖሊታን ሚዲያ ነው፡፡ ‘ተወዳዳሪ ሚዲያ እንሆናለን’ ስንልም ዋነኛ ተልኳችን በይዘት፣ በአቀራረብ፣ በቴክኖሎጂ እና በሰው ሃይል ነው፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ ብዙ ነገር እየተሰራ ነው” በማለት አስረድተዋል፡፡
“አዲስ አበባ ሁሉን አቀፍ እድገት እና ለውጥ እያሳየች ትገኛለች፡፡ ይህ ለውጥና እድገት ደግሞ በመዝናኛው፣ በትምርትና በሌሎችም መንገዶች ማህበረሰቡ ጋር መድረስ አለበት፡፡ እናም ‘ለማህበረሰቡ ድምጽ እንሆናለን፣ እያዝናናን፣ እናስተምራለን’ ስንል በንድፈ ሃሳብ ብቻም ሳይሆን በተጨባጭ ተግባራትና በስራዎቻችን ነው” ሲሉም አክለዋል፡፡
ይህ የዋና ስራ አስፈጻሚው ሃሳብ አንድሬ ገብርኤል ኒኮላ የተባሉ የዘርፉ ባለሙያ በሰሩት ጥናትም የተረጋገጠ ነው፡፡ አጥኝው “Popular Media as Entertainment-Education” በሚል ርእስ እ.ኤ.አ. በ2025 በሳተሙት ጥናት አንድ ሚዲያ አሳታፊ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን በመቅረጽ ማህበረሰቡን በማዝናናት፣ በማስተማር እና በማወያየት ለእድገትና ለሁሉን አቀፍ ለውጥ የማነሳሳት ኃላፊነት አለበት፡፡ ይህ ሲሆን በአንድ ሀገርና ከተማ ለውጥና እድገት እውን እንደሚሆን በጥናታቸው ጠቅሰዋል፡፡

የጃንኮ ፕሮዳክሽን መስራች ዋቆ ጌታቸው በበኩላቸው አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ከአዲስ አበባ ለውጥ ጋር አብሮ የሚራመድ ሚዲያ መሆኑንና አብሮ ለመስራት በመወሰናቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል። “ቡቤ” የተሰኘው አዲስ የኮሜዲ ሲትኮም በኤኤምኤን ፕላስ ሲቀርብ ለይዘትና ለጥራት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።
ድራማው እያዝናና የሚያስተምር እና በከተማ ያለውን ማህበራዊ መስተጋብር የሚያንጸባርቅ እንደሆነ የተናገሩት ዋቆ ጌታቸው፣ ከፕሮዳክሽን ጥራት አንጻር አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ያለው የቴክኖሎጂ አቅም አብሮ ለመስራት የሚያስችል ነው። ጊዜው የዲጂታል ዘመን እንደመሆኑ ከኤኤምኤን ፕላስ በተጨማሪ በዲጅታል ሚዲያም እንደሚለቀቅ አብራርተዋል፡፡
በእርግጥም በአንድ ግዙፍ ሜትሮፖሊታን ከተማ ውስጥ የሚኖር ማህበረሰብ ፍላጎት ዘርፈ ብዙ ነው። ነዋሪው መረጃን ብቻ ሳይሆን፣ ማንነቱን የሚገልጽ፣ የዕለት ተዕለት ውጥረቱን የሚያቃልልና የተስፋ ስንቅ የሚሆነው መዝናኛ ይሻል። አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ (AMN) ይህንን የከተማዋን ነባራዊ ሁኔታ በጥልቀት በመረዳት፣ ራሱን የ“የትውልድ ድምፅ” እና የ“ሜትሮፖሊታን ሚዲያ” ተምሳሌት አድርጎ እየገነባ ይገኛል፡፡
የሜትሮፖሊታን ሚዲያነት መገለጫው ዘመናዊነት፣ ተደራሽነትና ጥራት ነው። ተቋሙ ባለፉት ጥቂት ዓመታት የከተማዋን ወጣቶችና ልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የሚያሳትፉ ፕሮግራሞችን ቀርጾ ወደ ስራ ገብቷል። ይህ እንቅስቃሴ ደግሞ በሚዲያና በመዝናኛ ኢንዱስትሪው፣ በሚዲያውና በመዲናዋ ነዋሪዎች መካከል አዲስ ድልድይ እየገነባ ይገኛል።
ሚዲያው ለከተማዋ የጥበብ እድገት ካበረከታቸው ትላልቅ ስራዎች መካከል “አዲስ ታለንት ሾው” አንዱ ነው። ይህ ፕሮግራም መድረክ አጥተው ለነበሩ በርካታ ወጣት የጥበብ ባለሙያዎች ትልቅ በር የከፈተ ነበር። የ“አዲስ ታለንት ሾው” ስኬት ለተቋሙ መነቃቃትን ፈጥሮ፣ አሁን ደግሞ “ውብ አዲስ” የተሰኘ ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ ለህዝብ ለማድረስ በዝግጅት ላይ ይገኛል። “ቡቤ” ደግሞ ተጨማሪ የመዝናኛ አማራጭ ሆኖ ብቅ ብሏል፡፡ ይህም ተቋሙ ለከተማዋ እድገትና የነዋሪዎቿን የመዝናኛ ፍላጎት ለማሟላት ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ተግባር ነው፡፡
በጊዜው አማረ