አዲስ አበባ የኢትዮጵያ የዘመናዊ ኪነትና የከያኒያን መፍለቂያ፣ ማሳደጊያና መገናኛ ማዕከል በመሆን ለዓመታት ስታገለግል ቆይታለች፡፡ በተለይም እንደ ፒያሳና ደጃች ውቤ ያሉ አካባቢዎች ለበርካታ አስርት ዓመታት የዕውቅ ከያኒያን ዋነኛ መሰባሰቢያ በመሆን አገልግለዋል። እነዚህ ታሪካዊ መንደሮች፣ የከያኒያንና የተደራሲያን ቀጥተኛ መስተጋብር የሚስተዋልባቸው ስፍራዎች በመሆናቸው ለብዙ ዝነኛ የፈጠራ ሥራዎች መወለድ መነሻ መሆን ችለዋል። ዛሬም በኮሪደር ልማቱ አማካኝነት እነዚህ ስፍራዎች ታሪካዊ ገጽታቸውን ጠብቀው በዘመናዊ መልክ እንደገና ተገንብተዋል፡፡ የታላላቅ ከያኒያን መታሰቢያ ሐውልቶች በኖሩባቸው በእነዚህ አካባቢዎች በመሰራታቸው ሌላ ማራኪ ውበት ጨምረዋል፡፡ ከእነዚህ ከያኒያን መካከል ባለቅኔና ፀሃፌ ተውኔት ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድህን በሰባ ደረጃ አካባቢና ደራሲና ጋዜጠኛ ስብሃት ገብረ እግዚአብሄር በደጃች ውቤ ሰፈር መታሰቢያ ሀውልት ተሰርቶላቸዋል፡፡ የአዲስ ልሳን ዝግጅት ክፍልም በአይነታቸው ለየት ያሉ የከያኒያን መታሰቢያ ሃውልቶች በኖሩበት አካባቢ መሰራቱ ለኪነ ጥበብ ዘርፉ፣ ለተደራሲያንና ለመዲናዋ ያለው ፋይዳን አስመልክቶ አጭር ዳሰሳ አድርጓል፡፡
የጥበብ አውራዎችን ያከበረው መታሰቢያ
የደጃች ውቤ ሰፈር ታሪክ ሲነሳ የደራሲ ስብሃት ገብረ እግዚአብሔር ስም ቀድሞ መምጣቱ የማይቀር ጉዳይ ነው። ምክንያቱም ይህች ሰፈር በስብሃት የድርሰት ዓለም ውስጥ እንደ አንድ ታላቅ ገጸ-ባህሪ የምትታይ ማዕከላዊ ስፍራ ስለሆነች ነው። በተለይም ዝነኛው “ሌቱም አይነጋልኝ” የተሰኘው ልብ-ወለዱ፣ መቼቱንና አጠቃላይ የታሪክ ፍሰቱን ያደረገው በደጃች ውቤ ሰፈር ላይ ሲሆን፣ ወጣቱ ስብሃት በወቅቱ በዚህ ሰፈር እየተዝና የታዘባቸውና የኖራቸው ገጠመኞች ለድርሰቱ መፈጠር እንደ ዋነኛ ግብዓት አገልግለዋል። ዛሬ ስብሃት በተዝናናባት፣ ብዙ ህይወት ባሳለፈባትና የጥበብ መነሻው ባደረጋት ደጃች ውቤ ሰፈር ውስጥ የእርሱ መታሰቢያ ሐውልት ተሰርቶ ማየት፣ በደራሲውና በሰፈሩ መካከል ያለውን የማይበጠስ ኪነ ጥበባዊ ትስስር ለትውልድ የሚያስተላልፍ የታሪክ ምስክር ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡
በተመሳሳይ መልኩ፣ ለሌላኛው ባለቅኔና ፀሃፌ ተውኔት ለሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድህን በሰባ ደረጃ አካባቢ መታሰቢያ ሐውልት መሰራቱ ትልቅ ትርጉም ያለው ተግባር ነው። ሰባ ደረጃ ሎሬት ጸጋዬ ለበርካታ ዓመታት የኖረባትና በርካታ ታላላቅ የሥነ-ጽሑፍና የተውኔት ሥራዎቹን የጻፈባት ሰፈር ነች።
እነዚህ ሐውልቶች ከያኒያኑ በኖሩባቸውና አሻራቸውን ባሳረፉባቸው ሰፈሮች ውስጥ መሰራታቸው፣ ጥበብና ታሪክ ከቦታዎች ጋር ያላቸውን ቁርኝት ያሳያል። ይህም በኮሪደር ልማቱ አማካኝነት የከተማዋን ጎዳናዎች የታሪክና የኪነ-ጥበብ መዝገብ በማድረግ፣ አዲስ አበባ የጥበብ ሰዎች በስራቸውና በመታሰቢያቸው አማካኝነት የሚከበሩባት ሕያው ከተማ መሆኗን ያረጋግጣል።
ገጣሚ፣ ሃያሲና ጋዜጠኛ ዲበኩሉ አዛነው የኢትዮያ የኪነት ፈርጦች በእንዲህ ያለ መልኩ በአደባባይ መዘከራቸው ምን ፋይዳ አለው? ሲል የአዲስ ልሳን ዝግጅት ክፍል ላቀረበለት ጥያቄ የሚከተለውን መልሷል፤ እንደ ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድህን እና ደራሲ ስብሃት ገብረ እግዚአብሔር ያሉ የጥበብ ቁንጮዎች ሳቢ በሆነ መታሰቢያ ሐውልት መዘከራቸው ለኪነ ጥበብ ዘርፍ ትልቅ ትርጉም አለው። እነዚህ ከያኒያን በቃላት ቀለምነት የኳሏት አዲስ አበባ፣ ዛሬ በተሰራላቸው መታሰቢያ ሐውልቶች አማካኝነት ከትውልዱ ጋር ፊት ለፊት እንዲገናኙ ተደርጓል። ይህም ለኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች የተሰጠውን ክብር ከፍ የሚያደርግ ከመሆኑም በላይ፣ ወጣቱ ትውልድ ስለ ሀገሩ የኪነ ጥበብና የባህል ምሰሶዎች እንዲጠይቅና እንዲመራመር ያነሳሳል። ከያኒያኑ ከጥበብ አፍቃሪያን ልብ ባሻገር በአደባባይ ሐውልት መታሰባቸው፣ የከተማዋን የቱሪስት መስህብነት ያሳድጋል፡፡ አዲስ አበባም የባህልና የኪነ ጥበብ ማዕከል መሆኗን በግልጽ የሚያሳዩ ምስክሮች ናቸው ብለዋል፡፡
ለእነዚህ የኪነ ጥበብ ፈርጦች በአደባባይ መታሰቢያ ሐውልት ከተሰራላቸው በኋላ በርካታ የጥበብ አፍቃሪያን ወደ ስፍራው ተጉዘው ጉብኝት እያደረጉ ናቸው፡፡ ከከያኒያኑ ጋር ተቀምጠው ፎቶ በመነሳት በማህበራዊ የትስስር ገጻቸው የሚያጋሩት ፎቶ የዚህ አንዱ ማሳያ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ዕውቅ የጥበብ ሰዎች መታሰቢያ ሐውልቶቹን ከጎበኙ በኋላ የተሰማቸውን ስሜት በማህበራዊ የትስስር ገጻቸው አጋርተዋል፡፡ ከእነዚህ ከያኒያን መካከል ገጣሚና መምህር በድሉ ዋቅጅራ (ዶ/ር)፣ እንዲሁም ደራሲና ጋዜጠኛ ዘነበ ወላ ይገኙበታል፡፡
በድሉ (ዶ/ር) በፈረንጆቹ የካቲት 5 ቀን 2026 “በኑሯቸው ስራዎቻቸውን የበለጡ ጸሀፍያን” በሚል ርዕስ በማህበራዊ የትስስር ገጹ ባጋራው ጽሑፍ፣ “ያው! ውቤ በረሀ ተቀምጧል፡፡ …ስብሀት ድንቅ ጸሐፊ ነው፡፡ ዘወትራዊ ቃላትን ያስቀደመ የቋንቋ አጠቃቀሙ አንባቢን ይዞ ይፈስሳል፡፡ ገጸ ባህርያቱም የአንባቢ ጓደኛ ለመሆን ጊዜ አይወስዱም፡፡ . . . ስለስራዎቹ ብዙ ማለት ቢቻልም፣ ብዙ አልተባለም፡፡ ብዙ የተባለው ስለ ገድላዊ ኑሮውና መልክአዊ ገጽታው ነው፡፡ ይህ የሆነው አኗኗሩ ከስራው የበለጠ አስደናቂ በመሆኑና በዚህም የተነሳ በቅርብ የሚያውቁት ሰዎችና ደራስያን ከስራው ይልቅ ስለህይወቱ አልቀው ስለሚናገሩና ስለሚጽፉ ነው፡፡ …አሁን ስብሃትን በስራው ሳይሆን በኑሮው የሚያውቁትም አያጡትም፤ ያው ውቤ በረሀ ተቀምጧል” ሲል ከትቧል፡፡
የስብሃትን የህይወት ታሪክ የጻፈውና የስብሃት የቅርብ ወዳጅ የነበረው ደራሲና ጋዜጠኛ ዘነበ ወላ መታሰቢያ ሃውልቱን ከተመለከተ በኋላ ስሜቱን በማህበራዊ የትስስር ገጹ አጋርቷል፡፡ በፈረንጆቹ የካቲት 19 ቀን 2026 “መታሰቢያ አኖሩልህ!” በሚል ርዕስ የሚከተለውን ጽፏል፤ “እነሆ ጋሼ ስብሃት ለአብ ገብረ እግዚአብሔር ይህንን ዓለም በሞት ከተሰናበተ ድፍን 14 ዓመት ሆነው። መታሰቢያ የአዲስ አበባ አስተዳደር ካኖረለት አስራ አምስት ቀን ሆነው መሰለኝ። ሄጄ ጎብኝቼዋለሁ። የፊታችን ሚያዝያ 27 ቀን 90ኛ የልደቱ ቀኑ ነው። ይህ እለት ድርብ በዓል የምናከብርበት እለት ነው። ጋሽ ስብሃት ይህንን ስለሚያውቅ “የእኔን ልደት የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው የሚያከብርልኝ” ይል ነበር። “እለቱ የድል ቀን ነው። እኔም ከልቤ የማከብረውን ታላቅ ትውልድ (1920ዎቹ) የነበረው ትውልድ ለእኔ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ታላቁ ትውልድ ነው። የእለቱ እለት ከአባት አርበኞች ጋር የድሉ በዓልን አራት ኪሎ አክብሬ የጋሼን ልደት ደግሞ መታሰቢያው ዘንድ እገኛለሁ። የሞላላችሁ አብረን እንታደም…” ሲል ጥሪ ማቅረቡ ይታወሳል፡፡
ሐውልቶቹ ከመታሰቢያነት ባሻገር
የደራሲ ስብሃት ገብረ እግዚአብሔር እና የሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድህን መታሰቢያ ሐውልቶች፣ ከአዲስ አበባ የኮሪደር ልማት ጋር ተያይዞ ወደ አደባባይ መውጣታቸው ዘርፈ ብዙ ፋይዳ አላቸው። የሐውልቶቹን ጥበባዊ ይዘት፣ የማኅበራዊ መስተጋብር ፋይዳቸውና ለከተማዋ የሚሰጡት ገጽታ ከፍተኛ ነው።
እንደ ገጣሚ ዲበኩሉ ገለጻ ከሆነ፣ ሐውልቶቹ የቆሙበት አኳኋን ከባህላዊው “ሐውልት በከፍታ ላይ” የማቆም ስልት ወጥቶ፣ ከሕዝብ ጋር እኩል መድረክ ላይ መገኘታቸው ትልቅ የሥነ-ጥበብ ፋይዳ አላቸው። ሁለቱም ከያኒያን ወንበር ላይ ተቀምጠው ምስላቸው በሐውልት መልኩ መቀረጹ፣ ጥበብ ከሰማይ የወረደችና የማይደረስባት ምስጢር ሳትሆን፣ ከሰው ልጆች የዕለት ተዕለት ሕይወት ጋር የተቆራኘች መሆኗን ያሳያል። ይሄ አይነቱ ሕዝባዊ የጥበብ ስልት፣ የጥበብ አፍቃሪያን ከመታሰቢያ ሐውልቶቹ ጋር የቅርብ ወዳጅነት እንዲሰማቸውና ጥበብን እንደ ጓደኛ እንዲቀርቧቸው የሚያደርግ የፈጠራ ውጤት ነው።
ከተደራሲያን አንጻር ሲታይ፣ እነዚህ ሐውልቶች አንባቢው ከመጽሐፍ ገጾች ጋር ያለውን ግንኙነት በአካል ወደመገናኘት ስሜት ያሸጋግሩታል። አንድ ተደራሲ ከስብሃት ወይም ከጸጋዬ ሐውልት ጎን ተቀምጦ ፎቶ ሲነሳ ወይም ሲያርፍ፣ በሕይወት በነበሩበት ወቅት በነበራቸው መንፈስ ውስጥ የመሳተፍ ዕድል ያገኛል። ይህ አይነቱ ግንኙነት በተለይ ለወጣቱ ትውልድ ደራሲያኑን እንደ ታሪካዊ ሰው ብቻ ሳይሆን፣ እንደ አርአያና የቅርብ መካሪ እንዲመለከታቸው በማድረግ የንባብና የፈጠራ ፍላጎቱን ያነሳሳል ሲል ገጣሚ ዲበኩሉ አስተያየቱን አጋርቶናል።
በሌላ በኩል ደግሞ እነዚህ መታሰቢያ ሐውልቶች ከተማዋን “የታሪክና የጥበብ መዝገብ” ያደርጓታል። ጎብኚዎች በኮሪደሩ ላይ ሲንቀሳቀሱ የሚያገኟቸው እነዚህ መታሰቢያዎች፣ አዲስ አበባ የዘመናዊነትና የኪነጥበብ ማዕከል መሆኗን በጉልህ ይነግሯቸዋል። ሐውልቶቹ በተሰሩባቸው ስፍራዎች ላይ የሚፈጠረው ውበት፣ ከተማዋን ከስነ ውበት ባለፈ ጥልቅ የሆነ “የእይታ ማንነት” እንዲኖራት በማድረግ የዓለም አቀፍ ጎብኚዎችን ቀልብ ይስባሉ።
የመታሰቢያ ሐውልቶቹ ዲዛይን ከያኒያኑ በሕይወት ዘመናቸው ከነበራቸው ጠባይ ጋር የተቀራረበ መሆኑ ሌላኛው ጥበባዊ ጥንካሬ ነው። ስብሃት በነፃነትና በቀላል ሕይወት እንደሚታወቀው ሁሉ፣ ሐውልቱም ያንን ተዝናኖትና የሰላም መንፈስ በሚያሳይ መልኩ ተቀርጿል። ሎሬት ጸጋዬ ደግሞ በቁም ነገርና በጥልቅ ፍልስፍና የታወቀ እንደመሆኑ፣ ሐውልቱ የሚያንፀባርቀው ግርማ ሞገስና ትኩረት የእርሱን ባለቅኔያዊ ሰብዕና በሚገባ ይገልጻል። ይህ የአካልና የመንፈስ ውህደት ሐውልቶቹን ሕያው አድርጓቸዋል።
እነዚህ መታሰቢያ ሐውልቶች የቆሙባቸው አካባቢዎች እንደ “ክፍት ሙዚየም” ማገልገላቸው ለከተማዋ ነዋሪዎች የሥነ-ልቦና እርካታን ይሰጣል። ሰዎች በመንገድ ላይ ሲጓዙ ታላላቅ የጥበብ ሰዎችን እያዩ ማለፋቸው፣ በሀገራቸው የጥበብ ታሪክ ላይ ያላቸውን ኩራት ያሳድገዋል። ይህ ደግሞ በአካባቢው ላይ የባህልና የኪነ-ጥበብ ስሜት ጎልቶ እንዲታይ በማድረግ፣ ቦታዎቹ የደራሲያን መገናኛና የውይይት መድረኮች እንዲሆኑ በር ይከፍታል።
ከታሪካዊ ፋይዳ አንጻር፣ ሐውልቶቹ ከያኒያኑ በኖሩባቸውና በሰሩባቸው አካባቢዎች (ለምሳሌ ደጃች ውቤና ሰባ ደረጃ) መሰራታቸው ለቦታዎቹ “መንፈሳዊ ክብደት” ይሰጣቸዋል። አንድ ስፍራ በስም ብቻ ከሚታወቅ ይልቅ፣ እንዲህ ያሉ የጥበብ መታሰቢያ ሐውልት ሲኖሩት አንድም አካባቢው ይበልጥ እንዲታወቅ፤ በሌላ በኩል ደግሞ የከያኒው ታሪክ ጎልቶ እንዲታይ ያደርጋሉ። ይህም አዲስ አበባ የጥበብ ልጆቿን የምታከብርና ታሪኳን በጎዳናዎቿ ላይ የምትጽፍ ከተማ መሆኗን ለዓለም ያሳያል።
በአጠቃላይ እነዚህ የስብሃትና የጸጋዬ ሐውልቶች ከውበት ባለፈ የኢትዮጵያን የኪነ-ጥበብ ትላንት፣ ዛሬና ነገ የሚያስተሳስሩ ድልድዮች ናቸው። ሐውልቶቹ ለተደራሲያን የቅርብ ወዳጅ፣ ለከተማዋ የጥበብ ጌጥ፣ ለቱሪስቶች ደግሞ የታሪክ ማሳያ በመሆን ከፍተኛ አገልግሎት ይሰጣሉ። በኮሪደር ልማቱ ውስጥ እንዲህ ያሉ የኪነት አሻራዎች መጨመራቸው፣ የከተማዋ የጥበብ ማዕከልነት ይበልጥ ጎልቶ እንዲታይ የሚያደርግ ነው።
በአብርሃም ገብሬ