በምጥ ወይስ በቀዶ ህክምና መውለድ ይመከራል?

You are currently viewing በምጥ ወይስ በቀዶ ህክምና መውለድ ይመከራል?

AMN – የካቲት 27/2018 ዓ.ም

አሁን አሁን በብዙ እናቶች በኩል የመውለጃ ጊዜያቸው ሲደርስ አምጠውና ተጨንቀው ከመውለድ ይልቅ በቀላሉ በቀዶ ህክምና መውለድን አማራጭ የመሻት አዝማሚያዎች አየጨመሩ መምጣታቸው በባለሙያዎች በኩል ሲነገር ይደመጣል፡፡

እነዚህን ሁለት የወሊድ አማራጮች የትኞቹ ወላጆች በየትኛው መንገድ ቢጠቀሙ የተሻለ እንደሚሆን ከኤ ኤም ኤን ጋር ቆይታ ያደረጉት የፅንስና የማህፀን ህክምና ስፔሻሊስት ዶክተር ታከለ ጸጋዬ አብራርተዋል፡፡

በእናቶችና በፅንስ ጤና ላይ የሚከሰቱ ድንገተኛ አደጋዎችን ለመታደግ ቀዶ ህክምና የተሻለ አማራጭ ቢሆንም፣ አስጊ ጉዳይ ሳይኖር በምርጫ ብቻ የሚደረጉ ቀዶ ጥገናዎች የራሳቸው የሆነ የጤና ስጋት እንዳላቸው ዶክተር ታከለ ገልጸዋል፡፡

እንደ ዶክተር ታከለ ገለጻ በወሊድ ጊዜ የቀዶ ህክምና ስራ የሚሰራበት ዋናው ምክንያት ለእናቲቱ ወይም ለልጁ ጤና አስጊ ሁኔታዎች ሲፈጠሩ ብቻ ነው። ቀዶ ህክምና የሚደረገው በአንዳቸው ላይ ችግር ይኖራል ተብሎ ሲታሰብ እንጂ በሀኪሙ እና በእናትየዋ ፍላጎት ብቻ አይደለም ብለዋል።

እንደ ባለሙያው ገለጻ፣ በወሊድ ጊዜ የቀዶ ህክምና ስራዎች በሁለት ምክንያት ሊከናወኑ ይችላሉ፡፡ የመጀመረያው በፕሮግራም የሚሰራ ሲሆን ይህም ምጥ ከመጀመሩ በፊት አስቀድሞ በሚያዝ ቀጠሮ የሚከናወን ነው፡፡

በዚህ ሁኔታ የሚሰሩ እናቶች ከዚህ በፊት በማህፀናቸው ላይ የቀዶ ጥገና ተደርጎ እጢ የወጣላቸው ወይም ማህፀናቸው የተሰፋ ከሆነ፣ የደም ግፊትና የስኳር በሽታ ያለባቸው እናቶች ከሆኑ፣ የፅንሱ ክብደት ከመጠን በላይ ትልቅ ወይም የአቀማመጥ መዛባት ካለው፣ የእንግዴ ልጁ ከፊት ለፊት ከሆነ እንደሆነ ዶክተር ታከለ ተናግረዋል፡፡

ሌላኛው ምክንያት ምጥ ከጀመረ በኋላ በድንገት የሚሰሩ ሲሆን ይህም ምጡ በሂደት ላይ እያለ ለእናቲቱና ለፅንሱ ደህንነት ሲባል የሚደረግ የቀዶ ማዋለድ ህክምና ነው፡፡

ለዚህ ክስተት ከሚዳርጉ ምክንያቶች መካካል ደግሞ የማህፀን በር መከፈት መዘግየት ወይም የምጥ መራዘም፣ የልብ ትርታ መዛባት፣ ድንገተኛ የእንግዴ ልጅ መላቀቅና የደም መፍሰስ መሆናቸውን ዶክተሩ ለአብነት አንስተዋል፡፡

ዶክተር ታከለ አክለውም፣ በአሁኑ ወቅት ያለ ህክምና አስፈላጊነት በምርጫ ብቻ በቀዶ ህክምና የመውለድ ፍላጎት እየጨመረ ቢመጣም፣ የህክምና ክልከላ እስከሌለ ድረስ ተፈጥሯዊ በሆነ መንገድ በምጥ መውለድ እጅግ እንደሚመከር አስገንዝበዋል።

የቀዶ ማዋለድ ሂደት የራሱ የሆነ የማደንዘዣ ሂደት፣ የድህረ-ቀዶ ጥገና ህመም እና የደም መፍሰስ አደጋዎች እንዳሉትም ጠቁመዋል።

በምጥ ወቅት ምጥን የሚያነቃቃና የህመም ማስታገሻ ህክምና የሚሰጠው እናቶች ተፈጥሯዊ በሆነ መንገድ እንዲወልዱ ለማበረታታት ነው ያሉት ዶክተሩ፣ እናቶች በሰላም እንዲወልዱና ጤናማ ህፃናትን እንዲያቅፉ ለእናቶች ተገቢው ክትትል እየተደረገላቸው እንደሚገኝም ዶክተር ታከለ ጸጋየ ተናግረዋል፡፡

በፍሬሕይወት ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review