የቤቢ መሐመድ ዋቢ እና የጥቁር አንበሳ ባለሙያዎች ድንቅ ተጋድሎ

You are currently viewing የቤቢ መሐመድ ዋቢ እና የጥቁር አንበሳ ባለሙያዎች ድንቅ ተጋድሎ

AMN – ሚያዝያ 8/2018 ዓ/ም

በሕክምናው ዓለም ተስፋ መቁረጥና ተስፋ አለመቁረጥ መካከል ያለው መስመር እጅግ ቀጭን ነው።

በተለይም ገና በ25 ሳምንታት ዕድሜው፣ ከአንድ ኪሎ ግራም ባነሰ ክብደት ወደዚህች ዓለም ለሚመጣ ጨቅላ፣ ሕይወት ትልቅ ፈተና ናት።

ሆኖም በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የጨቅላ ህፃናት ጽኑ ህሙማን ክፍል (NICU) ውስጥ የተመዘገበው ውጤት፣ ከቴክኖሎጂ በላይ የሰው ልጅ ጥረትና የባለሙያዎች ቅንጅት ምን ያክል ተአምር መስራት እንደሚችል ዳግም አስመስክሯል።

ያልተጠበቀው የእናትነት ፈተና

የ36 ዓመቷ ወይዘሮ መኪያ ከማል ለሁለተኛ ጊዜ እናት ለመሆን በጉጉት እየተጠባበቀች ነበር።

ሆኖም እርግዝናዋ ገና ስድስት ወር ከአምስት ቀን (25 ሳምንት ከ5 ቀን) ላይ እያለ ባጋጠማት ድንገተኛ ህመም፣ ኮልፌ ቀራኒዮ ወደ ሚገኘው የግራር ጤና ጣቢያ ትሄዳለች፡፡

ባለሙያዎች ሁኔታው ከአቅማቸው በላይ መሆኑን ተረድተው ወደ ጥቁር አንበሳ ሲልኳት፣ የመኪያ ልብ በጭንቀት ተሞልቶ ነበር።

የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) መመሪያዎች እንደሚጠቁሙት፣ በዚህ ዕድሜና ክብደት የሚወለዱ ህጻናት የመኖር ዕድላቸው እጅግ አነስተኛና በሳይንሳዊ አገላለጽ “ውርጃ” ሊባሉ የሚችሉ ናቸው።

የባለሙያዎቹ ቆራጥነት

ሕጻን መሐመድ ዋቢ ሲወለድ ክብደቱ ገና 900 ግራም ብቻ እንደነበር ለኤ ኤም ኤን ዲጂታል የገለጹት በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የጨቅላ ህፃናት ፅኑ ህሙማን ክፍል ኃላፊ ነርስ ሲስተር ጠጄ ቱፋ፣ “ህጻኑን ስናየው ተስፋ የሚቆረጥበት ቢመስልም ባለሙያዎቻችን ግን እጃቸውን አልሰጡም” ይላሉ።

ህጻኑ እንደተወለደ ለ10 ደቂቃ የሚቆይ የልብና የመተንፈሻ ማነቃቂያ ተደረገለት።

ከዚያም ቀጣይነት ያለው አወንታዊ የመተንፈሻ ግፊት (CPAP) ድጋፍ እንዲያገኝ ተደርጎ ወደ ጽኑ ህሙማን ክፍል ገባ፤ እያንዳንዷ ሰከንድ ለሕጻኑ ሕልውና ወሳኝ ነበረች።

የሦስት ወራት ተጋድሎ

ለቀጣዮቹ ሦስት ወራት በጥቁር አንበሳ NICU ውስጥ የተካሄደው ርብርብ የሕክምና ብቻ ሳይሆን የሰብአዊነትም ጭምር ነበር።

ባለሙያዎቹ የሕጻኑን ሕይወት ከመታደግ ጎን ለጎን፣ ተስፋ የቆረጠችውን የእናት መኪያ ስነ-ልቦና ለመጠገን ሌት ተቀን ደከሙ።

የበዚህም የህጻኑ ክብደት፡ ከ900 ግራም ተነስቶ ወደ 1.8 ኪሎ ግራም አደገ፤ ከታህሳስ 7 ቀን እስከ መጋቢት 21 ቀን 2018 ዓ.ም ቆይታው በጽኑ ትግል ዘለቀ።

በመጨረሻም የዓይን፣ የጆሮ እና አጠቃላይ የአካል ምርመራዎች ምንም ዓይነት እንከን እንደሌለባቸው አረጋገጡ።

የደስታ እምባ እና ሽኝት

መጋቢት 21 ቀን 2018 ዓ.ም በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ልዩ ቀን ነበር፣ ያ በ900 ግራም ክብደት ሕልውናው አጠራጣሪ የነበረው ቤቢ መሐመድ፣ ሙሉ ጤነኛ ሆኖ በደመቀ ሁኔታ ወደ ቤቱ ተሸኘ።

እናት መኪያ በደስታ እምባ ታጅባ “ልጄን በሕይወት ወደ ቤቴ ይዤው እየገባሁ ነው! ብድራችሁን ከአላህ አግኙ” ስትል ባለሙያዎቹን መርቃለች።

የባለሙያዋ ምክር

እንዲህ ዓይነት አጋጣሚዎች እንዳይፈጠሩ ማንኛዋም ሴት ከእርግዝና በፊትና በእርግዝና ወቅት የሕክምና ክትትል ማድረግ ይገባታል ሲሉ ሲስተር ጠጄ ቱፋ ሙያዊ ምክርና መልእክት አስተላልፈዋል።

በያለው ጌታነህ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review