“የባህር በር ጥያቄው ለቀድሞ ሰራዊታችን ዳግም ትንሳኤ ነው” – የሀገር ባለውለታዎች

You are currently viewing “የባህር በር ጥያቄው ለቀድሞ ሰራዊታችን ዳግም ትንሳኤ ነው” – የሀገር ባለውለታዎች

AMN – መጋቢት 4/2018 ዓ.ም

ኢትዮጵያ ወደ ቀይ ባህር ለመመለስ የጀመረችው ዲፕሎማሲያዊ ጥረት፣ ለዓመታት በቁጭትና በባዶነት ስሜት ውስጥ ለቆዩ የቀድሞ የሀገር መከላከያ እና የባህር ኃይል አባላት አዲስ ተስፋን የፈነጠቀ መሆኑን የቀድሞ ወታደሮች ገለጹ።

ባለፉት አስርት ዓመታት የሀገሪቱን ሉዓላዊነት ለማስከበር ከአሰብ እስከ ምጽዋ፣ ከናቅፋ እስከ ከረን በጽናት የተዋጉት እነዚህ የቀድሞ ወታደሮች፤ ኢትዮጵያ ከባህር በር መገፋቷ የማይሽር ጠባሳ ሆኖባቸው መቆየቱን በምሬት ይናገራሉ።

በቀድሞው የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት አባል የነበሩት ሌተናል ኮሎኔል ወርቁ ገሰሰ፣ አሰብን ከጀብሃ ታጣቂዎች ነጻ ለማውጣት የተከፈለውን መራራ መስዋዕትነት ሲያስታውሱ፤ “ስለ ሀገር ዳር ድንበር ሲነሳ ውስጤ ይቃጠላል፤ የባህር በራችን መታጣት እንቅልፍ የነሳኝ ጉዳይ ነበር” ብለዋል።

የቀድሞ የባህር ኃይል አባል የነበሩት ሰብ ሌፍተናት አዱኛ ቃቂ በበኩላቸው፣ የባህር በር መነፈግን “አንገት እንደሌለው ሰው መሆን ነው” ሲሉ ይገልጹታል።

የባህር ኃይሉ መበተንና ሀገሪቱ ከባህር ዳርቻ መራቋ ለሙያዊ ክብራቸውም ሆነ ለሀገራዊ ማንነታቸው ትልቅ ባዶነት ፈጥሮባቸው መቆየቱን ጠቅሰዋል።

በግለሰቦች ሴራና በታሪክ አጋጣሚ ለዓመታት ተዳፍኖ የቆየው የባህር በር ጥያቄ አሁን ላይ በይፋ መነሳቱ፣ ዳግም እንደተወለዱ የሚቆጥሩት ሌላኛው የቀድሞ ወታደር አስራት ንጉሴ ናቸው። ይህ እንቅስቃሴ “ለቀድሞው ሰራዊት ትንሳኤ ነው” ሲሉ ደስታቸውን ገልጸዋል።

ቀይ ባህርና ዓባይ ለኢትዮጵያ ብልጽግና መሰረትና ከሀገሪቱ ህልውና ጋር የማይነጣጠሉ መሆናቸውን የገለጹት ባለውለታዎቹ፤ የአሁኑ ትውልድ የታላላቆቹን ታሪክ በመመርመርና ወቅታዊውን የዓለም ፖለቲካ በመገንዘብ፣ የባህር በርን የማስመለስ ጉዳይ የቀጣይ የቤት ስራው ሊያደርገው እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል።

በቶለሳ መብራቴ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review