AMM – መጋቢት 4/2018 ዓ.ም
የፊታችን ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ለሚካሄደው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በአዲስ አበባ ከተማ የሚወዳደሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ በከተማ ልማት ፖሊሲ አማራጮቻቸው ላይ ያተኮረ የሁለተኛ ዙር ክርክራቸውን በአዲስ ሚዲያ ኔትወርክ ስቱዲዮ አካሂደዋል።
በክርክሩ የተሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ብልጽግና ፓርቲ፣ ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት (ለኢትዮጵያ)፣ የወሎ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ወዴፓ) እና አዲስ ትውልድ ፓርቲ (አትፓ) ናቸው፡፡

በክርክሩም የብልጽግና ፓርቲ ባለፉት አምስት ዓመታት የተገበረው የከተማ ልማት ፖሊሲ የከተሞችን ገጽታና የነዋሪዎችን ኑሮ መለወጡን ገልጿል። በቀጣይም ከተሞችን ከገጠር ትራንስፎርሜሽን ጋር በማስተሳሰር የሥራ፣ የቱሪስት፣ የኢንዱስትሪና የፈጠራ ማዕከላት ለማድረግ እንደሚሠራ አስታውቋል።
ተፎካካሪ ፓርቲዎቹ በበኩላቸው፣ በከተማ መልሶ ማልማትና ማደስ ሂደት ላይ ይታያሉ ያሏቸውን ክፍተቶች በመጠቆም፣ ከገዢው ፓርቲ እንለይበታለን ያሏቸውን የፖሊሲ አማራጮች ለሕዝብ አቅርበዋል።

መድረኩ ፓርቲዎቹ የሕዝብን ድምፅ ለማግኘት ያስችሉናል ያሉዋቸውን ስትራቴጂዎች በማቅረብ ከፍተኛ ክርክር ያደረጉበት ነበር።

የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ የምርጫ ዴስክ ከፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ጋር በደረሰው ስምምነት መሠረት፣ በቀጣይም ፓርቲዎቹ በተደለደሉባቸው ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ተከታታይ የፖሊሲ ክርክሮችን ለተመልካች ማቅረቡን ይቀጥላል።
በአልዓዛር መኮንን