ሁሉም የሃይማኖት ተቋማት ጽንፈኝነትን እና አክራሪነት በጋራ ሊታገሉ ይገባል

You are currently viewing ሁሉም የሃይማኖት ተቋማት ጽንፈኝነትን እና አክራሪነት በጋራ ሊታገሉ ይገባል

AMN መጋቢት 7/2018 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር “የሃይማኖት ተቋማት በመደመር መንግስት እይታ” በሚል መሪ ሀሳብ በመዲናዋ ከሚገኙ የተለያዩ የሃይማኖት ተቋማትና አባቶች ጋር ምክክር እያካሄደ ይገኛል፡፡

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በመዲናዋ ከሚገኙ የእስልምና እምነት አባቶች ጋር የማጠቃለያ ምክክር ያካሄዱ ሲሆን ህዝበ ሙስሊሙም ሆነ ሌሎች ሃይማኖቶች እኩል እና በጋራ ሊታገሏቸዉ ይገባል ያሏቸዉን ጉዳዮች አንስተዋል፡፡

አንዳንድ የአለም ሃገራት በጽንፈኝነት እና አክራሪነት ምክንያት ለተለያዩ ማህበራዊ፤ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ቀዉሶች መዳረጋቸዉን እንደ ምሳሌ በማንሳት ሁሉም ሃይማኖቶች ጽንፈኝነትን እና አክራሪነትን እኩል እና በጋራ ሊታገሉ ይገባል ብለዋል፡፡

የእምነት አክቲቪዝም አለምን እያስቸገረ ያለ ጉዳይ በመሆኑ ሁሉም ሃይማኖቶች ያሉትን ችግሮች በሰለጠነ መንገድ እና በዉይይት መፈታት ይኖርባቸዋል፤ የሃይማኖት አባቶችም ሊከበሩ ይገባል፡፡

በሃይማኖት ስም በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች የሚተላለፉ ጽንፈኛና አክራሪ ይዘቶች ሀገርን፤ ተቋማትን እና ህዝቡን የሚጎዱ ስለሆነ ህዝቡ ለባዳም ለባንዳም እድል መስጠት የለበትም ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

ሁሉም የሃይማኖት ተቋማት አንድ ሃገር አላቸዉ፤ ከኢትዮጵያ ዉጪ ሌላ ሃገር የለንም ያሉት ከንቲባ አዳነች አቤቤ በሃገር ጉዳይ በእምነት መለያየት የለብንም፤ በጋራ እጅ ለእጅ ተያይዘን ልንቆም ይገባል ብለዋል፡፡

ከታሪክ ጋር የተያያዙ ችግሮችን በንግግር በፍታት እንደሚገባ ያስገነዘቡት ከንቲባዋ የሃይማኖት ተቋማትም ዉስጣዊ አንድነታዉን ማጠናከር እንደሚኖርባቸዉ አፅንኦት ሰጥተዋል፡፡

መከፋፈል የልማትና የሰላም አጀንዳ ሊሆን አይችልም፤ ሃይማኖቶች መከፋፈልን ሊያስወግዱ ይገባል፡፡

ከሃይማኖት ጋር በተያያዘ የቅሬታና የተበዳይነት ስሜት ሊኖር አይገባም ያሉት ከንቲባ አዳነች አቤቤ የሃይማኖት ተቋማትም ሆነ ቤተ እምነቶች ያልተመለሱላቸዉ ጥያቄዎች ሊኖራቸዉ ይችላል፤ ያሉትን ዉስንነቶች መረዳትና መገንዘብ ተገቢ ነዉ፤ የአንዱ ችግር ሲፈታ ሌላዉ ቅሬታ ዉስጥ መግባት የለበትም ብለዋል፡፡

የሃይማኖት ተቋማት ተከባብሮ እና ተቻችሎ የመኖር ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ እሴቶችን ሊጠናከሩ እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡

ከንቲባ አዳነች አቤቤ ህዝበ ሙስሊሙ የሰላም አምባሳደርነቱን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚኖርበትም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

በወንድማገኝ አሰፋ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review