ማህበረሰቡ በበዓላት ወቅት ብቻም ሳይሆን በማንኛውም ጊዜ ለራሱ ጤንነት ሲል አካባቢውን ከብክለት መጠበቅ እንዳለበት ተጠቁሟል
በዓላት በኢትዮጵያውያን ዘንድ ልዩ ትርጉም አላቸው፡፡ ፍቅር፣ አንድነት እና መረዳዳት የሚገለፅባቸው፣ ደምቀውና ደስታን ዘርተው የሚውሉ ቀናት ናቸው። ሆኖም በዓላትን ለማድመቅ የምናከናውናቸው ተግባራት የአካባቢ ብክለትን ጨምሮ ዘርፈ ብዙ ችግሮች እንዳያስከትሉ ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ በተለይ የሚታረዱ የእንስሳት ተረፈ ምርቶች፣ የቤት ውስጥ ቆሻሻዎች እና የፕላስቲክ ውጤቶች በአግባቡ ካልተወገዱ አየር እንዲበከል፤ ለተለያየ በሽታ እንድንጋለጥ፤ የውሃ ማፋሰሻ መስመሮች እንዲዘጉ… በማድረግ ለጉዳት ይዳርጋሉ፡፡ በአዲስ አበባም መሰል የበዓል ዝግጅት እንደሚደረጉና ተግባራቱ ነዋሪዎችን እና ከተማዋን ለተለያዩ ችግሮች እያጋለጡ እንደሆነ የዝግጅት ክፍላችን ካነጋገራቸው ሰዎች ያሰባሰበው መረጃ ያመላክታል፡፡
የከተማዋ ነዋሪ የሆኑት አቶ አደም ሙስጠፋ በጉዳዩ ላይ በሰጡት አስተያየት፣ “በዓላት ሲመጡ በደስታ ለማሳለፍ የተለያዩ ነገሮች ገዝተን ወደ ቤት እናስገባለን፡፡ ከእነዚህ ውስጥ በግ ማረድ ወይም ቅርጫ ማስገባት ይጠቀሳል። ለምሳሌ፡- እኔ ለዒድ አል ፈጥርም ሆነ አረፋ በዓል በግ አርዳለሁ፡፡ ከዚህ በፊት ፈርሱን እና ደሙን ቱቦ ውስጥ እንደፋዋለን፡፡ ይህም ለብዙ ቀናት ቱቦው ተደፍኖ ውሃ እንዳያልፍ ያደርግ ነበር። አሁን ግን ከዚህ ትምህርት በመውሰድ እንዳይሸትም ሆነ የፍሳሽ ማስወገጃ መስመሮች እንዳይዘጉ በግቢያችን ጥግ ላይ ጉድጓድ ቆፍረን መቅበር ጀምረናል” ይላሉ፡፡
“የእንስሳት ተረፈ ምርት አለአግባብ ውጭ ላይ ከተጣለ ዝንቦች እንዲራቡ ያደርጋል፤ ውሾችም ይበትኑታል” የሚሉት አቶ አደም ሙስጠፋ፤ ይህ እንዳይሆን ቆሻሻን በየቦታው ባለመጣልና በአግባቡ በማስወገድ ራሳችንን ከበሽታ፣ አካባቢያችንን ደግሞ ከብክለት እንጠብቅ ይላሉ፡፡
በበዓላትም ሆነ በመደበኛ ቀናት ቆሻሻን በአግባቡ እንደሚያስወግዱ የነገሩን ደግሞ ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ ወይዘሮ ሰላም ክፍሌ ናቸው። “ከወትሮው በተለየ በበዓላት ወቅት የቆሻሻ መጠኑ ይጨምራል፡፡ በዚህ ጊዜ ከዚህ በፊት እንደማደርገው የሚበሰብሱና የማይበሰብሱ በመለየት በቆሻሻ ማዳበሪያ ውስጥ አስቀምጣለሁ። የጽዳት ሰራተኞች ሲመጡም አውጥቼ እሰጣለሁ፡፡ ግቢ ውስጥ በግ በምናርድበት ወቅትም የታረደበትን ስፍራ በውሃና በበረኪና አፀዳለሁ” ሲሉ ቆሻሻን በአግባቡ በማስወገድ የራሳቸውንም ሆነ የቤተሰባቸውን ጤና እንደሚጠብቁ ተናግረዋል፡፡
በበዓላት ወቅት የሚደረጉ የእርድና መሰል ተግባራት አካባቢ ላይ ምን ያክል ተጽዕኖ እንደሚያሳድር እና ከማህበረሰቡም ምን እንደሚጠበቅ ማብራሪያ የሰጡት የአዲስ አበባ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን የአካባቢ ብክለት ክትትልና ቁጥጥር ተፅዕኖ ግምገማ ቡድን መሪ ወይዘሮ ሰናይት ተስፋዬ ናቸው፡፡ ቡድን መሪዋ በማብራሪያቸው እንደገለጹት፣ ከወትሮው በተለየ ከበዓላት ጋር በተያያዘ በየቤቱ የሚታረዱ እንስሳት ቁጥር ይጨምራል፡፡ በዚህም ፈርስ፣ ቆዳ፣ ደም እና ቀንድ የመሳሰሉ ተረፈ ምርቶች ይመነጫሉ፡፡
የተለያዩ እቃዎች የሚገዙባቸው ማሸጊያዎች፣ ቤታችንን የምናስውብባቸው ነገሮች፣ የመጠጥ ጠርሙሶችና ሃይላንዶች፣ ከሽንኩርት ልጣጭ ጀምሮ እስከ ቄጤማ ያለው ተረፈ ምርት በከፍተኛ መጠን ይመነጫል፡፡ እነዚህ ተረፈ ምርቶች በአግባቡ ካልተወገዱ ከፍተኛ የብክለት ምንጭ ይሆናሉ። በባህላችን ለበዓላት ሰዎች ሰብሰብ ብለው ቅርጫ ይከፋፈላሉ፡፡ ይህም አብዛኛውን ጊዜ በህጋዊ መንገድ ወይም በቄራዎች ሳይሆን ሰፈር ውስጥ በህገ ወጥ መንገድ ነው እርድ የሚከናወነው፡፡ ከታረዱት እንስሳት የሚወጣውን ተረፈ ምርት አንዳንድ የማህበረሰብ ክፍሎች ውሃ ማፋሰሻ መስመሮች (ቱቦዎች) ውስጥ ይደፋሉ፡፡ ይህ ሲሆን የከተማዋን የፍሳሽ ማስወገጃዎች ይዘጋሉ። እነዚህ የፍሳሽ ማስወገጃዎች ከተዘጉ ደግሞ ዝናብ በሚዘንብበት ወቅት መተላለፊያ ስለሚያጣ የጎርፍ አደጋ ያስከትላል፡፡
ከዚህ ባለፈም መጥፎ ጠረን ስለሚያመጣ ለዝንብና መሰል ነፍሳት መራቢያ ይሆናል፡፡ የውሃ ብክለት ይፈጥራል። የአካባቢን እይታም ያስተጓጉላል፡፡ ይህ እንዳይሆን በተቻለ መጠን እርድ ሲከናወን በህጋዊ መንገድ ማከናወን፣ የሚመለከተው አካልም ሌሎች ቆሻሻዎችን በአግባቡ ሰብስቦ እንዲያነሳ በጥንቃቄ ማስቀመጥ ተገቢ መሆኑን ቡድን መሪዋ ገልጸዋል፡፡
“ብክለትን መከላከል ከቤትና ከአካባቢ ይጀምራል” ያሉት ወይዘሮ ሰናይት፤ ይህን ማህበረሰቡ ተግባራዊ እንዲያደርገው የአዲስ አበባ ከተማ አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን በዋናነት ትኩረት ሰጥቶ ግንዛቤ ፈጠራ ላይ እየሰራ ነው፡፡ ይህም ሲባል አጠቃላይ በከተማዋ በተለያየ ጊዜ ግንዛቤ ይሰጣል፡፡ በተገኘው መድረክ ሁሉ ለአካባቢ ብክለት የሚያጋልጡ ነገሮች ምን እንደሆኑ፣ በምን መንገድ መወገድ እንዳለባቸው እንዲሁም የሚያስከትሉት ጉዳት ጭምር እንዲያውቁ የማድረጉ ስራ እየተሰራ ነው፡፡ በመደበኛ እቅድ በዘንድሮው በጀት ዓመት በስምንት ወራት ውስጥ በተለያዩ አካባቢያዊ ጉዳዮች ላይ ለ112 ሺህ 518 የህብረተሰብ ክፍሎች በገፅ ለገፅ የግንዛቤ ፈጠራ ስራ ተሰርቷል፡፡ ከንቅናቄ ስራዎች አንጻር ከ2017 ዓ.ም ጀምሮ በወንዝ ብክለት መከላከል ለ1 ሚሊዮን 408 ሺህ 693፣ በፅዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ ለ1 ሚሊዮን 67 ሺህ 161 የህብረተሰብ ክፍሎች የገፅ ለገፅን ጨምሮ በተለያዩ መንገዶች ግንዛቤ ተፈጥሯል፡፡
ግንዛቤ ፈጠራው በክፍለ ከተማ፣ በወረዳ እና በብሎክ ቤት ለቤት፣ በቅስቀሳ እንዲሁም በብሮሸር ጭምር ይሰጣል። በዚህ መሰረት የፍሳሽ፣ የአየር፣ የሽታ እንዲሁም የድምፅ ብክለት ደረሰብን ብለው የሚመጡ አቤቱታዎች መቀነስ መቻላቸው እና የከተማዋ አብዛኞቹ አካባቢዎች ንፁህ መሆናቸው ውጤታማ ለመሆናችን ምስክር ናቸው፡፡ ከዚህ በፊት ብክለት ሲያጋጥም የት ማመልከት እንኳን እንዳለባቸው ግንዛቤው ያልነበራቸው የማህበረሰብ ክፍሎች አሁን ግንዛቤው አላቸው፡፡
ሌላኛው ብክለት ሲያጋጥም በ6713 ነፃ የስልክ መስመር ደውለው እንዲያሳወቁ ተደርጓል፡፡ በዚህ መስመርም ማህበረሰቡ ደውሎ ያሳውቃል፤ ያጋጠሙ የብክለት ችግሮችን ይናገራል፡፡ ህብረተሰቡም አካባቢው ተበክሎ እያየ ዝም አይልም፡፡
በአሁኑ ወቅት የላስቲክ አጠቃቀማችን እየቀነሰ መጥቷል ያሉት ወይዘሮ ሰናይት፤ ማህበረሰቡ በበዓላት ወቅት ብቻ ሳይሆን በማንኛውም ጊዜ ቆሻሻ ጎድጓዳ ቦታዎች እንዲሁም ወንዝ ዳር ከመጣል መከልከል አለበት፡፡ ምክንያቱም በተለይ እንደ አዲስ አበባ የፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦዎች ከተዘጉ ጎርፉ አደጋ የሚያደርሰው እራሱ ነዋሪው ላይ ነው፡፡
እንደ ቡድን መሪዋ ገለጻ፣ መስሪያ ቤቱ ከአዲስ አበባ ፅዳት አስተዳደር ኤጀንሲ፣ ከደንብ ማስከበር ባለስልጣን፣ ከውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን፣ አዲስ አበባ ፖሊስ እንዲሁም ከአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ጋር እየሰራ ይገኛል፡፡ አዳዲስ መረጃዎች ሲኖሩም ለእነዚህ አካላት በማሳወቅ ለማህበረሰቡ እንዲያደርሱ እየተደረገ ይገኛል፡፡
ማህበረሰቡ በበዓላት ወቅት ብቻ ሳይሆን በማንኛውም ጊዜ ለራሱ ጤንነት ሲል አካባቢውን ከብክለት መጠበቅ እንዳለበት የሚናገሩት ወይዘሮ ሰናይት፤ የእንስሳት እርድን በህጋዊ መንገድ መፈፀም፣ ክፍት ቦታዎችና ቱቦዎች ባሉበት ቦታዎች ጨለማን ተገን አድርጎ ቆሻሻን ከመጣል መቆጠብ ተገቢ እንደሆነ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
የከተማዋ ንፅህና እና የማህበረሰቡ ጤና እንዲጠበቅ እንዲሁም ሳቢና ማራኪ ሆና እንድትታይ ከአዲስ አበባ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ጋር በቅንጅት እንደሚሰሩ የነገሩን ደግሞ በአዲስ አበባ ከተማ ፅዳት አስተዳደር ኤጀንሲ የአገልግሎት አሰጣጥ ዳይሬክተር አቶ ግርማ ኃይሉ ናቸው፡፡ ኤጀንሲው በዓመቱ ውስጥ ያሉ በዓላትንና የአደባባይ ሁነቶችን ታሳቢ በማድረግ ዓመታዊ ዕቅዶችን ያቅዳል። በእቅዱ መሰረትም ማህበረሰቡ በምን መንገድ ቆሻሻን እንደሚያስወግድ ግንዛቤ ይፈጥራል፡፡
ዳይሬክተሩ እንደገለፁት፤ በበዓላትም ይሁን በሌሎች ጊዜያት ማህበረሰቡ የሚያመነጨውን ቆሻሻ በአግባቡ እንዲይዝና እንዲያስወግድ በየተቋማቱና ቤት ለቤት የግንዛቤ ስራ እየተሰራ ነው፡፡ ከዚህ ባለፈም ኤጀንሲው የሚሰራቸውን ስራዎች በዶክመንተሪ መልክ በአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ እናስተላልፋለን፡፡ የአዲስ አበባ ደንብ ማስከበር ባለስልጣንም ግንዛቤ በመስጠትና ግንዛቤው ኖሯቸው ቆሻሻን በአግባቡ የማይዙና የማያስወግዱ ሲኖሩ ተጠያቂነትን በማስፈን እገዛ ያደርግልናል፡፡ ስራዎችን በቅንጅት መስራት የስራ ጫናን ያቀልላል። ለከተማዋም ፅዳት ትልቅ አስተዋፅኦ ያደርጋል፡፡ ከዚህ በፊት በቀን ሶስት ጊዜ ይሰበሰብ የነበረውን ቆሻሻን በአሁኑ ወቅት ምሽትንም በመጨመር አራት ጊዜ እንዲሰበሰብ ተደርጓል። ይህ ስራ ከተማዋ አሁን ያለችበትን ገፅታ እንድትይዝና ቱሪስቶችን የምትስብ እንድትሆን አድርጓታል ነው ያሉት አቶ ግርማ፡፡
በበዓላት ወቅት የእንስሳት እርድና መሰል ተረፈ ምርቶች በየቦታው እንዳይጣሉ ለየት ባለ ሁኔታ የየወረዳዎችና ክፍለ ከተሞች ፅዳት አስተዳደር ፅህፈት ቤቶች በቋሚነት ግንዛቤውን ይፈጥራሉ። ትናንት ለተከበረው የዒድ አል ፈጥር በዓልም ይህንኑ ነው ያደረግነው። በዚህም ግንዛቤው ሳይኖረው ከ10 ዓመት በፊት ተረፈ ምርቶችን በየወንዙና መንገድ ዳርቻዎች የሚጥል ማህበረሰብን ማስቀረት ተችሏል፡፡
በከተማዋ 76 በመቶ የሚሆነው ቆሻሻ የሚመነጨው ከመኖሪያ ቤትና አካባቢ መሆኑን የነገሩን አቶ ግርማ፤ ስለዚህ ህብረተሰቡ ከዚህ በፊት የሚያደርገውን ቆሻሻን በአግባቡ የመያዝና የማስወገድ ተግባር ወደፊትም አጠናክሮ ይቀጥል ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በፋንታነሽ ተፈራ