AMN – ነሐሴ 1/2018 ዓ.ም
የቁልፍ መሰረተ ልማቶች የሳይበር ደህንነት አዋጅ ቁጥር 1426/2018 ተግባራዊ ለማድረግ፣ የቁልፍ መሰረተ ልማት ባለቤት የሆኑ ተቋማት በአንድ አመት የሽግግር ጊዜ ውስጥ አስፈላጊውን የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ማጠናቀቅ እንደሚጠበቅባቸው የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር በሰጠው መግለጫ አስታወቋል።
አዋጁ ሙሉ በሙሉ ወደ ስራ ከመግባቱ በፊት ተቋማት የሰው ኃይላቸውን ማብቃት እና የቴክኖሎጂ ስርአቶቻቸውን ደህንነት ማረጋገጥ እንዳለባቸው መግለጫውን የሰጡት የኢመደአ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ትዕግስት ሃሚድ ገልጸዋል።
የቁልፍ መሰረተ ልማት ባለቤት የሆኑ ተቋማት በአጭር ጊዜ ውስጥ የሰለጠነ የሰው ኃይል ማደራጀት፣ ዘመናዊ፣ አስተማማኝ እና የሳይበር ጥቃቶችን መከላከል የሚያስችሉ የቴክኖሎጂ መሳሪያዎችን እና ሶፍትዌሮችን ማሟላት፣ የስርአቶችን ደህንነት ማረጋገጥ እና ድክመቶችን መለየት እንዲሁም የማስፈጸሚያ ማዕቀፍ ማዘጋጀት እንዳለባቸው ዋና ዳይሬክተሯ ገልጸዋል።
ተቋማት ማድረግ ካለባቸው ዝግጅቶች ጎን ለጎን አዋጁ ሙሉ በሙሉ ወደ ስራ በሚገባበት ጊዜ ተግባራዊ የሚሆኑ የውስጥ አሰራር ማዕቀፎች ተዘጋጅተው ወደ ስራ መግባታቸውን ገልፀዋል።
አዲሱ አዋጅ ለቁልፍ መሰረተ ልማት ባለቤቶች ከአደጋ ስጋት ምዘና እስከ ሳይበር ኦዲት ሰርተፊኬት ማግኘት ድረስ ያሉ 18 ዋና ዋና የሳይበር ደህንነት ግዴታዎችን ያስቀመጠ ሲሆን፣ አዋጁ በ12 የቁልፍ መሰረተ ልማት ዘርፎች ላይ ተግባራዊ ይሆናል።
እነዚህን ቁልፍ መሰረተ ልማቶች ለመለየት የተለያዩ ሀገራት ተሞክሮዎች መወሰዳቸው እና ሰፊ ዳሰሳ መካሄዱን ተናግረዋል።
ቴሌኮም፣ ፋይናንስ፣ ፀጥታ፣ ትራንስፖርት እና ትምህርት ቁልፍ ተብለው ከተለዩ ዘርፎች መካከል ናቸው።
በተጨማሪም የሳይበር ደህንነት ጥበቃን፣ ምርምርን እና የአቅም ግንባታን በዘላቂነት ለመደገፍ የሚያስችል “የቁልፍ መሰረተ ልማቶች የሳይበር ደህንነት ፈንድ” መቋቋሙን ገልፀዋል።
የሳይበር ደህንነት የሀገር ህልውና በመሆኑ የመገናኛ ብዙሃን ህብረተሰቡን በማንቃት፣ ሀሰተኛ መረጃዎችን በመዋጋት እና የተቋማትን ዝግጅት በመከታተል ሀገራዊ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞው እንዲሳካ ግንባር ቀደም ሚናቸውን እንዲጫወቱ ጥሪ ቀርቧል።
በአሰግድ ኪዳነማሪያም