AMN- መጋቢት 12/2018 ዓ.ም
የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ 31ኛ ሳምንት መርሐግብር ዛሬም ቀጥሎ አራት ጨዋታዎች ይከናወናሉ። ሊቨርፑል በአሜክስ ስታዲየም ቀን 9:30 ብራይተንን የሚገጥምበት ጨዋታ ከፍ ያለ ትኩረት አግኝቷል።
በሜዳው የሚጫወተው ብራይተን ሰሞነኛ ብቃቱ ጥሩ ነው። የፋብያን ኸርዝለር ቡድን በሊጉ ካደረጋቸው አራት የመጨረሻ ጨዋታዎች በአርሰናል ብቻ ተረትቶ ሦስቱን አሸንፏል። ሊቨርፑል በአንፃሩ በመጨረሻ ሁለት የሊግ ጨዋታዎቹ በዎልቭስ ተሸንፎ ከቶተንሃም ሆትስፐርስ ጋር አቻ ተለያይቷል።
ቻምፒየንስ ሊግ የሚያሳትፈውን ደረጃ ለመያዝ እየታገለ የሚገኘው ሊቨርፑል የዛሬ ጨዋታ ድል በእጅጉ ያስፈልገዋል። ከ30 ጨዋታዎች 49 ነጥብ የሰበሰበው የመርሲሳይዱ ክለብ 5ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ቼልሲ ወደ ሂል ዲኪንሰን ስታዲየም አቅንቶ ኤቨርተንን ምሽት 2:30 ይገጥማል። በፓሪሰን ዠርማ በድምር ውጤት 8ለ2 ተሸንፎ ከአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ውጪ የሆነው ቼልሲ በሁሉም ውድድር ሦስት ተከታታይ ጨዋታዎችን ተሸንፏል።
በክለቡ የጥቂት ወራት እድሜ ብቻ ያስቆጠረው አሰልጣኙ ሊያም ሮሲኒዮር ከወዲሁ ጫና ውስጥ ገብቷል። ቼልሲ አሁን ላይ በ48 ነጥብ 6ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
ምሽት 12 ሰዓት ፉልሃም ከ በርንሌይ ፣ ምሽት 5 ሰዓት ደግሞ ሊድስ ዩናይትድ ከ ብሬንትፎርድ የሚያደርጓቸው ጨዋታዎች የዛሬ መርሐግብር አካል ናቸው።
በሸዋንግዛው ግርማ