AMN – መጋቢት 12/2018 ዓ.ም
በልጆች የዕድገት ሒደት ላይ የሚታዩት ዳውን ሲንድረም እና ኦቲዝም ምንም እንኳን ሁለቱም የዕድገት ውስንነቶች ቢሆኑም በመንስዔያቸውም ሆነ በባሕሪ መገለጫዎቻቸው እጅግ የተራራቁ መሆናቸውን የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
እነዚህን ልዩነቶች ጠንቅቆ ማወቅ ለልጆቹ የሚደረገውን ድጋፍ ውጤታማ ለማድረግ ቀዳሚው ተግባር ነው።
የአዕምሮ ዕድገት ውስንነት (ዳውን ሲንድረም) መከሰት በቀጥታ ከሰውነት የዘረ መል (ክሮሞዞም) ቁጥር መዛባት ወይም በሳይንሳዊ አጠራሩ ከክሮሞዞም መብዛት ጋር የተያያዘ ነው።
በተለይም በ21ኛው ክሮሞዞም ላይ የሚፈጠር ተጨማሪ ቅጂ በልጆች ላይ ግልጽ የሆኑ አካላዊ መገለጫዎችን ያስከትላል።
ከነዚህም መካከል ጠፍጣፋ የፊት ገጽታ፣ በአንገት አካባቢ የሚታይ ድርብርብ ቆዳ፣ ጠበብ ያሉ ዓይኖች፣ የጡንቻ መላላት፣ ወጥ የሆነ የመዳፍ መስመር እንዲሁም የአንገት ማጠርና የሰውነት ክብደት መጨመር በዋናነት የሚጠቀሱት ናቸው፤ ሁኔታው በሕክምና ምርመራ በቀላሉ ሊታወቅ የሚችልም ነው።
በአንጻሩ የኦቲዝም መከሰት ትክክለኛ መንስዔ እስካሁን በውል ባይታወቅም፤ በአንጎል አወቃቀር እና በነርቭ ሥርዓት ዕድገት ልዩነት ምክንያት እንደሚመጣ ይታመናል።
ኦቲዝም እንደ ዳውን ሲንድረም በግልጽ የሚታይ አካላዊ መልክ የሌለው በመሆኑ በኦቲዝም ጥላ ስር የሚኖር ልጅ ከሌሎች እኩዮቹ ጋር ተመሳሳይ አካላዊ ገጽታ አለው።
ከማኅበራዊ ግንኙነት አንጻር ሲታይም ሁለቱም ሁኔታዎች ተቃራኒ ባሕሪን ያንጸባርቃሉ።
ዳውን ሲንድረም ያለባቸው ልጆች በአብዛኛው ተግባቢና ከሰዎች ጋር መገናኘት የሚወዱ ሲሆኑ፤ የሌሎችን ስሜት የመረዳት ከፍተኛ ፍላጎትና በማኅበራዊ ሕይወት ውስጥ በቀላሉ የመቀላቀል ዝንባሌ አላቸው።
በተቃራኒው ኦቲዝም ያለባቸው ልጆች በማኅበራዊ መስተጋብር ላይ ትልቅ ፈተና ይገጥማቸዋል።
ከአዲስ ሰው ጋር ዓይን ለአይን መገጣጠም ሊከብዳቸው የሚችል ሲሆን፣ ስሜታቸውን የመግለጽም ሆነ የሌሎችን ማኅበራዊ መስተጋብሮች የመረዳት ውስንነት ስለሚታይባቸው ብዙ ጊዜ ብቸኝነትን ይመርጣሉ።
የመግባቢያ ክሕሎትን በተመለከተም የጎላ ልዩነት ይታያል። ዳውን ሲንድረም (የአዕምሮ ዕድገት ውስንነት) ያለባቸው ልጆች የንግግር ዕድገት ቢዘገይባቸውም ሃሳባቸውን ለመግለጽና ለመግባባት ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ።
በኦቲዝም ረገድ ግን የንግግር ክሕሎት ከሰው ሰው የሚለያይ ሲሆን፣ አንዳንዶቹ በጭራሽ የማይናገሩ ሌሎቹ ደግሞ ከፍተኛ የቋንቋ ዕውቀት ቢኖራቸውም ያንን ዕውቀት ለማኅበራዊ ግንኙነት የመጠቀም ችግር ይስተዋልባቸዋል።

በተጨማሪም ኦቲዝም ያለባቸው ልጆች ተደጋጋሚ ድርጊቶችን ማዘውተርና ለከፍተኛ ድምጽ ወይም ለብርሃን ስሜታዊ የመሆን ባሕሪ ይታይባቸዋል።
በትምህርት ረገድ ዳውን ሲንድረም ያለባቸው ልጆች የመማር ፍጥነታቸው አነስተኛ ቢሆንም፣ በዕይታ የታገዙ ትምህርቶችን የመረዳት የተሻለ ብቃት ግን አላቸው።
በሌላ በኩል የኦቲዝም ተለዋዋጭ ባሕሪ ያለባቸው ልጆች በሒሳብ፣ በሥዕል ወይም በሙዚቃ ዘርፍ ልዩ ተሰጥዖ ሊኖራቸው ስለሚችል፤ የሚሰጣቸው ድጋፍ በባህሪ ለውጥ ሥልጠና ላይ ትኩረት ማድረግ እንዳለበት ባለሙያዎች ይመክራሉ።
አልፎ አልፎ አንድ ልጅ ሁለቱም ሁኔታዎች በአንድ ላይ ሊያጋጥመው ይችላል። በዚህ ወቅት ወላጆች የልጆቻቸውን ባህሪ በትኩረት በመከታተል የባለሙያ ድጋፍ እንዲያገኙ ማድረግ ይኖርባቸዋል።
በበረከት ጌታቸው