በመዲናዋ 24 ሰዓት፤ በሳምንት ሰባት ቀን መስራት ባህል እየሆነ መጥቷል
አዲስ አበባ በሰሉ እጆች ጥረት ልክ እንደ ስሟ ውብና አበባ እየሆነች መጥታለች፡፡ መንገዶቿ የሚያሳሱ፣ ፅዱ፣ ውብና ንፁህ ሆነዋል፡፡ ህንፃዎች፣ አረንጓዴ ስፍራዎች፣ ዘመናዊ የመንገድ መብራቶች፣ የተሽከርካሪ ማቆሚያዎች ልዩ ገፅታንና ውበትን አላብሰዋታል፡፡ ወንዞች ወደ ቀደመው ወዝና ማንነታቸው ተመልሰዋል፡፡
አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ፣ የአፍሪካ መዲናና በዓለም አቀፍ ደረጃ ሶስተኛዋ የዲፕሎማሲ ማዕከል ብትሆንም ከጥቂት ዓመታት በፊት የነበራት መሰረተ ልማት፣ የምታቀርበው አገልግሎት፣ የከተሜነት ደረጃዋ ስሟንና ሚናዋን የሚመጥን አልነበረም፡፡ በብዙ የከተሜነት መለኪያዎች ወደኋላ ቀርታ እንደነበር ማንም የማይክደው ሀቅ ነው። ይህንን ሁኔታ ለመቀየር፣ ለነዋሪዎች እና ጎብኚዎች ምቹ የሆነች ከተማ ለማድረግ ሀገራዊ ለውጡ ከመጣ ጀምሮ የተለያዩ ተነሳሽነቶችን በመንደፍ ሲሰራ ቆይቷል፡፡
ቀደም ሲል ተሽከርካሪን ማዕከል አድርገው የተሰሩ ጠባብ መንገዶች፣ ኋላቀር የፍሳሽና የቆሻሻ አወጋገድ፣ ያልዘመኑ የመንገድ መብራቶች፣ የመጥፎ ሽታና በሽታ ምንጭ የነበሩት ወንዞች የከተማዋ መገለጫ ነበሩ፡፡ በኮሪደር ልማት የተሽከርካሪ፣ እግረኛና ሳይክል መንገዶች ምቹ ሆነው ተሰርተዋል፡፡ የመኪና ማቆሚያዎች፣ የመንገድ ዳርቻ ማረፊያዎች፣ የህዝብ መናፈሻዎች፣ ደረጃቸውን የጠበቁ የመንገድ መብራቶች፣ ሰው ሰራሽ ፏፏቴዎችና ሌሎች ልማቶችን በማካተት ተሰርተዋል። እንደ ፒያሳ፣ አራት ኪሎ፣ ሽሮ ሜዳ፣ መገናኛ፣ ሲኤምሲ፣ ጎሮ፣ ሜክሲኮ፣ ሳሪስን ጨምሮ በርካታ አካባቢዎች ውበትን ተላብሰዋል፡፡
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) “ከተሜ፣ ከተሜነት፣ ክትመትና የኮሪደር ልማት” በሚል ርዕስ በቅርቡ አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክን ጨምሮ በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን በተላለፈው ቃለ ምልልሳቸው፣ “አዲስ አበባ በስም ብቻ ነበረች፡፡ ዛሬ ግን ስም ብቻ አይደለም። አብባለች፤ ነጽታለች፡፡ ማበቧ ስሟ ብቻ ሳይሆን መገለጫዋ ሆኗል፡፡ ይህንን ያመጣው የኮሪደር ልማት ነው” ብለዋል፡፡
አዲስ አበባ ትላልቅ ፕሮጀክቶችን፣ የህዝብ አገልግሎት መስጫ ህንጻዎችን በመገንባትም ሆነ የኮሪደርና የወንዝ ዳርቻ ልማቶችን በፍጥነት፣ በጥራትና በአጭር ጊዜ እንድታከናውን ያደረጋት ከአዳዲስ የስራ ባህል ጋር መተዋወቋ ነው፡፡ በቀን ብቻ ሳይሆን በሌሊት፣ በመደበኛ ብቻ ሳይሆን 24 ሰዓት፣ በሳምንት ሰባት ቀን የሰው ሀይልና ማሽነሪዎችን በማንቀሳቀስ መስራትን ባህል አድርጋለች፡፡
ከዚህም ጋር አብሮ ያልተቆራረጠ የአመራር ክትትል ሥራዎችን በፍጥነት ማጠናቀቅ እንዲቻል ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡ ከተማዋ ባለፉት ዓመታት ከፍተኛ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያላቸው በርካታ ፕሮጀክቶችን በመጀመር በ60፣ በ90፣ በ120 ቀናትን ጨምሮ በአጭር ጊዜ በፍጥነት እያጠናቀቀች ትገኛለች፡፡ የመንግስት አገልግሎት መስጫ ቢሮዎች፣ የጤና ተቋማት፣ ትምህርት ቤቶች፣ ፖሊስ ጣቢያዎች፣ የስፖርት ሜዳዎች፣ የህጻናት መጫወቻና ሌሎች ፕሮጀክቶችም ተገንብተው ለአገልግሎት ክፍት ሆነዋል፤ እየሆኑም ይገኛሉ፡፡
ወረታው በዛብህ (ዶ/ር) የአዕምሮ ኢንተርፕርነርሺፕ ማስፋፊያ አገልግሎቶች አክሲዮን ማህበር ሥራ አስኪያጅና የሥራ ፈጠራ አሰልጣኝ ናቸው፡፡ ጃፓን ብዙ የተፈጥሮ ሀብትና ለም የሚታረስ መሬት ሳይኖራት፤ ብዙ የምትሸጠው ነገር ፈጥራ፣ በዓለም ላይ ሶስተኛውን ግዙፍ ኢኮኖሚ መገንባት ችላለች፡፡ ለዚህም ያላት ጠንካራ የስራ ባህል ትልቁን ሚና ተጫውቷል፡፡ እንደ ደቡብ ኮሪያ፣ ሲንጋፖር፣ ማሌዥያ ያሉ የሩቅ ምስራቅ ሀገራት ጠንካራ የሥራ ባህል ካላቸው ሀገራት ተርታ እንደሚመደቡ ያነሳሉ፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት በአዲስ አበባ የተሰሩት የአንድነት እና እንጦጦ ፓርኮች፣ የወዳጅነት አደባባይ፣ የሳይንስ ሙዚየም፣ የዓድዋ ድል መታሰቢያ፣ በኮሪደር ልማት መሠረተ ልማቶችን በማዘመን የተሰሩ ሥራዎች ውብና ለማየት የሚያጓጉ ናቸው። የአዲስ አበባን ገፅታም በእጅጉ የቀየሩ መሆናቸውን ወረታው (ዶ/ር) ያነሳሉ፡፡ “ፕሮጀክቶቹ በአጭር ጊዜና በጥራት የተጠናቀቁ ከመሆናቸው ባሻገር የአዲስ አበባን ገፅታ በእጅጉ የቀየሩ ናቸው፡፡ ውበት ብቻ ሳይሆን ገቢን የሚፈጥሩ፣ የከተማዋን የወደፊት ህይወትና እንቅስቃሴ ታሳቢ ያደረጉ ናቸው፡፡ እነዚህ ዓይነት ሥራዎች በብዙ ዓመታት አይተናቸው የማናውቃቸው ናቸው፡፡” ሲሉም የተገኘው ውጤት የሚደነቅ እንደሆነ ያነሳሉ፡፡ በአዲስ አበባ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ለተገኘው ውጤት አዲስ የሥራ የባህል ለውጥ መኖሩና የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) እና የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ጨምሮ የአመራሩ የቅርብ ክትትልና ድጋፍ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡
በመጣው አዲስ የሥራ ባህል ለውጥ ለማሳካት ከተያዙ ሥራዎች መካከል በከተማዋ የሚታየውን የመኖሪያ ቤት ፍላጎት ለማርካት ከሶስት ወራት በፊት የተጀመሩ የቤቶች ልማት ግንባታ ፕሮጀክቶች ይጠቀሳሉ፡፡ በዘንድሮው ዓመት ብቻም በአዲስ አበባ 100 ሺህ ቤቶችን ለመገንባት ታቅዶ በ18 ሳይቶች የግንባታ ሥራዎች እየተከናወነ ይገኛል፡፡ የአዲስ አበባ ቤቶችና አስተዳደር ልማት ቢሮ አማካሪ ኢኒጂኒዬር አውራሪስ ከበደ ከሶስት ወራት በፊት ለአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ በሰጡት ማብራሪያ፣ የተያዘውን ሰፊ የሆነ እቅድ ለማሳካት እየተለመደ የመጣው በቀን ሃያ አራት ሰዓት፤ በሳምንት ሰባት ቀናት የመስራት የሥራ ባህል ወሳኝነት አለው፡፡ ከዚህ ቀደም ባለ 14 ወለል ያላቸው 24 ህንጻዎች ከዘጠኝ ወራት ባነሰ ጊዜ ማጠናቀቅ ከተቻለበት ተሞክሮ በመውሰድና ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም በፍጥነት ለማጠናቀቅ እየተሰራ ነው፡፡
የቤቶችን ለአብነት አነሳን እንጂ ቀንና ሌሊት በመስራት በፍጥነትና በጥራት በርካታ ፕሮጀክቶች ተገንብተው እየተጠናቀቁ ይገኛሉ፡፡ አዲስ አበባ በቀን ብቻ ሳይሆን በሌሊት የሥራ እንቅስቃሴዎች የሚከናወኑባት፣ በርካታ ወጣቶች በሥራ ዕድል ፈጠራ ተጠቃሚ የሚሆኑባት፣ በየጊዜው ፕሮጀክቶች የሚመረቁባት፣ የተነቃቃች፣ የሥራ፣ የመኖሪያና የመዝናኛ ከተማ ሆናለች፡፡ በቅርብ ዓመታት ያለውን ብናነሳ እንኳን በ2017 በጀት ዓመት ብቻ በአዲስ አበባ ከተማ በመንግስትና ኅብረተሰብ ተሳትፎ ከ19 ሺህ በላይ ፕሮጀክቶች ተጠናቅቀው ለአገልግሎት በቅተዋል፡፡ በ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያው ግማሽ ዓመትም 12 ሺህ በላይ ኘሮጀክቶችን ማከናወን እንደተቻለ የአዲስ አበባ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ከወራት በፊት ለአዲስ አበባ ምክር ቤት ካቀረቡት ሪፖርት መረዳት ይቻላል፡፡
ጠንካራ የሥራ ባህል መኖሩ በጊዜ ርዝመት ምክንያት የሚፈጠሩ የፕሮጀክትና የአገልግሎት መጓተቶችን በማስቀረትና በዚህ ምክንያት ያስከትል የነበረውን የዋጋ ንረት በመቀነስ ለከተማዋ እድገት ትልቅ አስተዋፅኦ እያበረከተ ይገኛል፡፡ የልደታ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ህንጻ ከአንድ ዓመት በፊት ተገንብቶ ለአገልግሎት በበቃበት ወቅት የአዲስ አበባ ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች ባደረጉት ንግግር፤ “በከተማችን ውስጥ ተጀምረው የማያልቁ ፕሮጀክቶች ተፈልገው እስከማይገኙ ድረስ፣ ድሮ ተጀምረው የተረሱትን ሳይቀር እያፈላለግን እየጨረስን፣ አዳዲሶችን በፍጥነት ጀምረን በፍጥነት እየጨረስን ነው፡፡ ይህም የሥራ ባህልን እያዳበረ፣ ወጪን እየቀነሰ፣ ለህዝብ ልማት መዋል የሚገባውን በጀት መቆጠብ እያስቻለ ነው” ብለዋል፡፡
ከንቲባዋ ከአንድ ወር በፊትም በካዛንቺስ እየተገነባ ያለውን የህፃናት ዓለም ማዕከልና በቦሌ መድኃኒዓለም አካባቢ የሚገነቡ የኮሪደር ልማት አገናኝ መስመሮችን የምሽት የሥራ እንቅስቃሴ ተዘዋውረው በጎበኙበት ወቅት፤ የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮች በምሽት ሥራዎች በሚከናወኑበት ስፍራ ተገኝቶ ያሉበት ደረጃን በመመልከት የመደገፍ፣ ውሳኔ የመስጠት፣ ከፍጥነትና ጥራት አኳያ ችግሮች ካሉም ወዲያውኑ እንዲስተካከሉ በማድረግ በተቀመጠላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ እየተደረጉ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ለኢዜአ በሰጡት ማብራሪያ፤ የኮሪደር ልማት እሳቤ በአዲስ አበባና ሌሎች የሀገሪቱ ከተሞች ተስፋ ሰጪ ለውጦችን ማምጣቱን በመጥቀስ፣ “አመራሩ ከቢሮ ወጥቶ በየመንገዱ ያሉ ችግሮችን እያየና እየፈታ የመሄድ ልምምድ መጀመራችን ከተሞቻችን የሚገባቸውን መልክ እንዲይዙ በእጅጉ እያገዘ ነው፡፡” ሲሉ እየተደረገ ያለው ክትትልና ድጋፍ ያስገኘውን አበርክቶውን አብራርተዋል፡፡
ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች በማህበራዊ የትስስር ገጻቸው ሰሞኑን ባስተላለፉት መልዕክት፣ “ከተማችን እየተገበረች ባለችው ሁለንተናዊ ልማት ለሁሉም የምትመች፣ ሁሉንም በፍትሐዊነት የምታገለግል፣ ማንንም ያልዘነጋች የአካታች ልማት ማሳያ ከተማ እያደረግናት ነው። ለሕፃናት፣ ለወጣቶች፣ ለአረጋውያንና ለአካል ጉዳተኞች፣ ለእግረኛው፣ ለባለ መኪናውና ለባለ ሳይክሉ የትራንስፖርት አማራጮችንና መሠረተ-ልማቶችን በፍትሐዊነት ያመቻቸች፤ ለስማርት ከተማነት፣ ለአገልግሎት አሰጣጥ፣ ለሸማቹ፣ ለባለሀብቱ፣ ለንግድና ለኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታን የፈጠረች እና የኮፍረንስ ቱሪዝም ማዕከል ከተማ እየሆነች ነው።” ብለዋል
በአዲስ አበባ ፕሮጀክቶችን ቀንና ሌሊት ሰርቶ በማጠናቀቅ፣ የንግድ እንቅስቃሴዎችን በምሽት ጭምር የሚካሄዱበት ምቹ ሁኔታ በመፍጠር የሚሰራው ስራ ከፍተኛ ለውጥ እያመጣና ለሌሎች ከተሞች ተምሳሌት የሆነ ሥራ መሆኑን ያነሱት ወረታው (ዶ/ር)፣ እስከአሁን ወደኋላ የቀረንበትን ለማካካስ፣ በከተሞች የሚታዩ ውስብስብ ችግሮችን ለማቃለልና ምርታማነትን ለማሳደግ የሥራ ባህሉን ህዝባዊ ማድረግ ላይ መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
በጥቅሉ ሀገራዊ ለውጡ ከመጣ ወዲህ ባለፉት ስምንት ዓመታት የኢትዮጵያ፣ የአፍሪካና የዓለም የዲፕሎማሲ መዲናዋ አዲስ አበባ በከፍተኛ ደረጃ ተለውጣለች፡፡ ይህንንም ነዋሪዎቿ ብቻ ሳይሆን አፍሪካውያን፣ ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች የመጡ፤ የቀድሞ ገፅታዋን የሚያውቋት አሁን ያሳየችውን ለውጥ እያነፃፀሩ በማድነቅ ሲናገሩና ሲጽፉ መስማት አዲስ አይደለም፡፡ በአዲስ አበባ በኮሪደርና በወንዝ ዳርቻ ልማት፣ በርካታ ሰው ተኮር ፕሮጀክቶችን በቀን ብቻ ሳይሆን በሌሊትም በማከናወን በአጭር ጊዜና በጥራት በማጠናቀቅ የተሰሩ ሥራዎች የከተማዋን ገፅታ ከመቀየር ባለፈ ለኢትዮጵያና ለአፍሪካ ከተሞች በምሳሌነት የሚጠቀስ ነው፡፡
በስንታየሁ ምትኩ