7ኛው ጠቅላላ ምርጫን አስመልክቶ አዲስ አበባ ለሚገኙ ዲፕሎማቶችና ዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች ገለጻ ተሰጠ

You are currently viewing 7ኛው ጠቅላላ ምርጫን አስመልክቶ አዲስ አበባ ለሚገኙ ዲፕሎማቶችና ዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች ገለጻ ተሰጠ

AMN – ግንቦት 17/2018

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ፣ በመጪው ሰኞ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ/ም የሚካሄደውን 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ አስመልክቶ፣ ተቀማጭነታቸውን አዲስ አበባ ላደረጉ የውጭ ሀገራት ዲፕሎማቶችና የዓለም አቀፍ ድርጅት ተወካዮች ገለጻ ሰጥተዋል።

ሰብሳቢዋ በገለጻቸው ስለ ምርጫው ዝግጅት፣ ስለ መራጮች ምዝገባ፣ ስለ ሴቶችና ወጣቶች ተሳትፎ፣ ስለ ደህንነት ዝግጅቶች እና ስለ ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ዝርዝር ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን፤ የምርጫ ሂደቱ ግልጽ፣ ነፃ እና ተዓማኒ እንዲሆን ከተለያዩ ተቋማት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ስለመሆኑም አስረድተዋል።

ለዚሁ ምርጫ ከ50 ሚሊዮን በላይ መራጮች መመዝገባቸውንና 52,029 የምርጫ ጣቢያዎች መቋቋማቸውን በመግለጽ፤ ለተፈናቃዮች፣ ለወታደሮችና ለተማሪዎች ልዩ የምርጫ ጣቢያዎች መዘጋጀታቸውን እንዲሁም የምርጫ ድምፅ መስጫ ካርዶች ለሁሉም የምርጫ ጣቢያዎች መሰራጨታቸውን አብራርተዋል።

በተጨማሪም ምርጫው ሰላማዊ፣ አሳታፊ እና ነፃ እንዲሆን ቦርዱ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሠራ መቆየቱን ገልጸዋል።

በገለጻው መክፈቻ ላይ የኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርሃኑ ጸጋዬ ባደረጉት ንግግር፣ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በተከታታይ ሲደረጉ የቆዩ ምርጫዎች ቀጣይ መሆኑን ገልጸው፤ ይህም በሀገሪቱ ለተጀመረው የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ መሠረት የጣለ መሆኑን አብራርተዋል።

ከገለጻው በኋላ በተደረገው ውይይት፣ የየተለያዩ ሀገራት እና የዓለም አቀፍ ድርጅት ተወካዮች ምርጫው ሰላማዊና አሳታፊ እንዲሆን ስለተደረገው እንቅስቃሴ በቂ ግንዛቤ ማግኘታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለኤ ኤም ኤን ያላከው መረጃ ያመለክታል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review