ኢትዮጵያ ከባህር በር ተነጥላ መኖር አትችልም – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)

You are currently viewing ኢትዮጵያ ከባህር በር ተነጥላ መኖር አትችልም – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)

AMN- ሚያዚያ 7/2018ዓ.ም

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ የባህር በር ማጣቷ በሀገሪቱ የኢኮኖሚ እድገት፣ በብሔራዊ ደህንነት እና በዜጎች የዕለት ተዕለት ሕይወት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እያሳደረ መሆኑን ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኢቢሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ የወደብ አልባነትን ችግር ገመና አልባነት ሲሉ የገለጹት ሲሆን፣ ጉዳዩ ከፖለቲካ ባለፈ የህልውና ጥያቄ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።

ኢትዮጵያ የራሷ የወደብ ባለቤት አለመሆኗ የዲጂታል ሉዓላዊነቷን አደጋ ላይ እንደሚጥል ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጠቀሱት።

የዲጂታል ፋይበር ኦፕቲክስ መስመሮች በሌሎች ሀገራት በኩል ማለፋቸው የሀገርን ሚስጥር ለመጠበቅ አስቸጋሪ ያደርገዋል ያሉት ጠቅላይ ሚንስትሩ፣ ይህም ሀገሪቱን ዲጂታል ገመና አልባ እንደሚያደርጋት አስረድተዋል።

በተጨማሪም ወደ ሀገር የሚገቡና የሚወጡ ምርቶች በሙሉ በሌሎች ሀገራት ቁጥጥር ስር መውደቃቸው የንግድ ሚስጥርን እንደሚያጠፋ ጠቁመዋል።

የወደብ አልባነት ችግር በእያንዳንዱ ዜጋ ኪስ ላይ ጫና እያሳደረ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብራርተዋል። የሎጂስቲክስ ወጪ ከጎረቤት ሀገራት አንጻር ከ50 እስከ መቶ በመቶ እንደሚበልጥ ነው የጠቀሱት።

አንድ ምርት ከሌላ ሀገር ተገዝቶ ናይሮቢ ከሚሸጥበት ዋጋ ይልቅ ኢትዮጵያ ውስጥ ሲሸጥ ቢያንስ የ30 በመቶ ጭማሪ እንደሚያሳይ ተናግረዋል። ይህም በዜጎች ላይ የሚታየውን የዋጋ ግሽበት እና የኑሮ ውድነት በቀጥታ እንደሚወስነው ነው ያብራሩት።

ኢትዮጵያ የባህር በር ማግኘቷ ለራሷ ብቻ ሳይሆን ለቀጣናው ሰላምም ወሳኝ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስገንዝበዋል።

ኢትዮጵያን የመሰለ ትልቅ ሀገር ከባህር በር ጉዳይ ርቆ ከሄደ፣ ትናንሽ ሀገራት የቀይ ባህርን ሰርጥና የንግድ መስመር የመጠበቅ አቅም ስለማይኖራቸው ለዓለም ንግድም ስጋት ይሆናል ብለዋል።

መንግስታቸው በአጭር ጊዜ መፍትሄነት በጅቡቲ እና በሞጆ አካባቢ የንግድ ቀጣናዎችን፣ የደረቅ ወደቦችን እና የባቡር መስመሮችን በማቀላጠፍ ወጪን ለመቀነስ እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

ሆኖም ግን ዘላቂው መፍትሄ በንግግር እና በሰጥቶ መቀበል መርህ የባህር በር ባለቤት መሆን ነው ሲሉ አስረድተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ከባህር በር ተነጥላ እስከወዲያኛው ትኖራለች ብሎ የሚያስብ ካለ እሱ የዋህ ነው በማለትም፣ ጉዳዩ ለሀገሪቱ ብልጽግና የማይታለፍ ቁልፍ ማነቆ መሆኑን አረጋግጠዋል።

በታደሠ ሽፈራው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review