ሚስ ወርልድ ኢትዮጵያ ሩት ይርጋለም የኢትዮጵያ የባህልና ጥበባት አምባሳደር ሆና ተሾመች

You are currently viewing ሚስ ወርልድ ኢትዮጵያ ሩት ይርጋለም የኢትዮጵያ የባህልና ጥበባት አምባሳደር ሆና ተሾመች

AMN-ሚያዚያ 21/2018 ዓ.ም

የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የ2018 የሚስ ወርልድ ኢትዮጵያ አሸናፊዋ ሩት ይርጋለምን የኢትዮጵያን ባህልና ጥበባት እና ብሔራዊ ጥቅሟን በዓለም አቀፍ መድረክ እንድታስተዋውቅ የባህልና ጥበባት አምባሳደር አድርጎ ሾሟታል።

በሚኒስቴሩ የኪነጥበብና ስነ ጥበብ ፈጠራ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ነብዩ ባዬ(ረ/ፕ) ሹመቱን አስመልክተው ለሚዲያ አካላት መግለጫ ሰጥተዋል።

ሚኒስትር ዴኤታው በሰጡት መግለጫ፣ የቁንጅና ውድድሮች ከመልክና ገፅታ በዘለለ የሀገራትን ባህል፣ ቱሪዝም እና ብሔራዊ ስኬቶችን ለዓለም የሚያስተዋውቁበት ትልቅ መድረክ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የአምባሳደርነት አደራና ኃላፊነት አሸናፊዋ ሩት ይርጋለም የተሰጣት አምባሳደርነት ሀገራዊ ገፅታን በመገንባት፣ ያላትን ተሰሚነት በመጠቀም የሰላም ስራዎችን መስራትና ማህበራዊ ችግሮችን ለመፍታት ጥረት ማድረግ እንዳለባት ሚኒስትር ዴኤታው አብራርተዋል።

የኢትዮጵያን ዘርፈ ብዙ ባህሎች፣ ሙዚቃና ትወናን በዓለም መድረክ በማቅረብ ሥራዎቿን እንደምትሰራ ገልፀዋል።

ሚኒስትር ዲኤታው ባለፈው ዓመት አሸናፊ የነበረችው ሀሴት ደረጀ በቆይታዋ የሀገሪቱን የልማት እንቅስቃሴዎች በማስተዋወቅ ረገድ ውጤታማ ስራ ማከናወኗን አስታውሰው፣ አዲሷ አምባሳደርም ይህንኑ ተልዕኮ እንድትቀጥል አሳስበዋል።

ሩት ይርጋለም በቬትናም በሚካሄደውና ከ170 በላይ ሀገራት በሚሳተፉበት 73ኛው የሚስ ወርልድ ውድድር ላይ ኢትዮጵያን ትወክላለች።

ወደ ውድድሩ ከመሄዷ በፊት ባሉት ሶስት ወራት ውስጥ የተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎችን በመጎብኘት ባህሎችንና ታሪካዊ ቦታዎችን እንድታጠና ሁኔታዎች በመንግስት እንደሚመቻችላት ሚኒስትር ዲኤታው ነብዩ ባዬ ገልፀዋል።

ሚስ ሩት ይርጋለም የተጣለባትን አደራ ለመወጣትና ሀገሯን በዓለም መድረክ በአግባቡ ለማስተዋወቅ ዝግጅቷን ማጠናቀቋን መግለጿን ከባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review