AMN – ሚያዝያ 22/2018 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባለፉት ዘጠኝ ወራት የመኖሪያ አካባቢዎችን በማሻሻልና ለዜጎች ክብር የሚመጥኑ የልማት ሥራዎችን በማከናወን ረገድ ውጤታማ ተግባራት ማከናወኑን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
የአስተዳደሩ የ2018 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት የሥራ አፈጻጸም ግምገማ በተካሄደበት ወቅት እንደተገለጸው፤ በመዲናዋ ደረጃቸውን የጠበቁ ዘመናዊ መኖሪያ ቤቶችን አጠናቆ ለነዋሪዎች ማስተላለፍ ተችሏል።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በወቅቱ ባደረጉት ንግግር እንዳመለከቱት፤ ከዚህ ቀደም በአዲስ አበባ ከተማ 74 በመቶ የሚሆነው አካባቢ በሽርፍራፊ ቆርቆሮና በጭቃ የተገነባ ጎስቋላ መንደር የነበረ ሲሆን፣ ባለፉት አምስት ዓመታት በተከናወኑ የተቀናጁ የልማት ሥራዎች ይህንን ቁጥር ወደ 30 በመቶ ዝቅ ማድረግ ተችሏል።

ይህም በከተማዋ ለረጅም ዓመታት የነበረውን የጎስቋላ መንደሮች ገጽታ በከፍተኛ ደረጃ የቀየረ ስኬት መሆኑን አብራርተዋል።
እነዚህ ተገንብተው ለነዋሪዎች የተላለፉ መኖሪያ ቤቶች የውሃ ማፋሰሻ መስመሮች፣ የንጹሕ መጠጥ ውሃ፣ የኤሌክትሪክ ኃይልና ሌሎች አስፈላጊ መሠረተ ልማቶች የተሟሉላቸው መሆኑን ከንቲባዋ ገልጸዋል።
ይህም ቀደም ሲል በነበሩ ጎስቋላ መንደሮች ውስጥ በተደጋጋሚ ይከሰት የነበረውን የእሳት አደጋ ሥጋት ከመቀነሱም በላይ ለነዋሪዎች ምቹና ጤናማ የመኖሪያ አከባቢ መፍጠር አስችሏል።
የልማት ሥራው ከመኖሪያ ቤት አቅርቦት ባለፈ የአካባቢውን ገጽታ በማዘመን የከተማዋን ውበት መለወጡን የገለጹት ከንቲባዋ፤ ነዋሪዎች ዘመናዊ የአኗኗር ዘይቤን እንዲለማመዱና ማኅበራዊ መስተጋብራቸው የሚጠናከርበት ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠር ማድረጉን ገልጸዋል።

ከዚህም በተጨማሪ የተከናወኑት የከተማ ማዘመን ሥራዎች አዲስ አበባ ለአህጉራዊና ለዓለም አቀፋዊ ተቋማት ተመራጭ የዲፕሎማሲ ማዕከል እንድትሆን ከማስቻላቸውም በላይ ለቱሪዝም ዘርፍ ዕድገት የላቀ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑን አስታውቀዋል።
በየክፍለ ከተሞቹ እየተከናወኑ የሚገኙት እነዚህ ዘመናዊ የመኖሪያ ቤቶች ግንባታና የከተማ ማዘመን ሥራዎች አዲስ አበባ ልዩ ገጽታና ውበት እንድትጎናጸፍ ማድረጋቸውንም ከንቲባ አዳነች አቤቤ ጨምረው ገልጸዋል።
በሻምበል ምሕረት