“አሊ ቢራ፤ ከድሬዳዋ እስከ ዓለም አቀፍ መድረኮች”

You are currently viewing “አሊ ቢራ፤ ከድሬዳዋ እስከ ዓለም አቀፍ መድረኮች”

አርቲስት አሊ መሐመድ ቢራ መስከረም 15 ቀን 1940 ዓ.ም በድሬዳዋ ከተማ ገንደ ቆሬ ተወለደ። ገና የሦስት ዓመት ሕፃን እያለ ወላጆቹ በመለያየታቸው በአባቱ እጅ ያደገው አሊ፣ በልጅነቱ የአገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ሙዚቃዎችን በማዳመጥና ለቤተሰቦቹ በማንጎራጎር ነበር የሙዚቃ ፍቅሩን ያሳየው።

በድሬዳዋ ከተማ ለነበረው የብዙ ቋንቋዎች ተናጋሪነት ምቹ ሁኔታ ምስጋና ይግባውና በአረብኛ፣ በአፋን ኦሮሞ ፣ በአደርኛና በሶማሊኛ ቋንቋዎች ሙዚቃዎችን የመጫወት አቅም ነበረው።

የአሊ ቢራ የሙዚቃ ጉዞ በይፋ የጀመረው በ1954 ዓ.ም ገና በ13 ዓመቱ የኦሮሞን ሙዚቃ ለማስተዋወቅ የተቋቋመውን “አፍረን ቀሎ” የተሰኘውን የሙዚቃ ቡድን በመቀላቀል ነበር። “አሊ ቢራ” የሚለው መጠሪያ ስምም የመጣው በዚሁ ቡድን ውስጥ እያለ ለመጀመሪያ ጊዜ ካቀነቀነው “ቢራ ዳ ባሪ” (Birraa dha Barihee) ከተሰኘው ተወዳጅ ዘፈኑ ነው።

በኋላም በክቡር ዘበኛ ኦርኬስትራና በአይቤክስ ባንድ ውስጥ በመጫወት ድንቅ የሙዚቃ ተሰጥዎውን በማስመስከር የኢትዮጵያ ሙዚቃ አብሪ ኮከብ ለመሆን በቅቷል።

አሊ ቢራ ከድምፃዊነቱ ባሻገር ዜማ ደራሲ፣ የግጥም ጸሐፊ፣ የሙዚቃ መሣሪያዎች ተጫዋችና አቀናባሪ የነበረ ሁለገብ ሙዚቀኛ ነው። በሙያ ዘመኑ 267 የሚደርሱ ራሱ ያቀናበራቸው የሙዚቃ ሥራዎችን ለአድማጭ ያደረሰ ሲሆን፣ ለታዋቂዎቹ ጥላሁን ገሠሠና መሐሙድ አህመድ ጭምር ዜማዎችን ሰጥቷል።

ሙዚቃዎቹ በዋናነት በአፋን ኦሮሞ ቋንቋ የቀረቡ ቢሆኑም፣ መልዕክቶቻቸው ግን ስለ ፍቅር፣ ስለ ሰው ልጅ መብት፣ ስለ እኩልነትና ስለ ሰላም የሚያጠነጥኑ ዓለም አቀፋዊ ይዘት ያላቸው ነበሩ።

ለኢትዮጵያ ኪነ-ጥበብ ላበረከተው ከፍተኛ አስተዋፅኦ ከጅማና ከድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲዎች የክብር ዶክትሬት ዲግሪ የተሰጠው አርቲስት አሊ ቢራ፣ ለ56 ዓመታት በሙዚቃ ዓለም ውስጥ አገልግሏል።

ለረጅም ዓመታት በስደት በውጭ አገር ቆይቶ ወደ አገሩ ከተመለሰ በኋላ ጥቅምት 27 ቀን 2015 ዓ.ም በ75 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል። አሊ ቢራ በሙዚቃው የዘራው የአንድነትና የመብት ትግል ዘሮች ዛሬም ድረስ በትውልድ ዘንድ እንደ ትልቅ ቅርስ ይከበራሉ።

በህሊና ፍቃዱ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review