AMN – ነሐሴ 1/2018 ዓ.ም
ሰላም የሚያሸብረው የህወሃት ቡድን ዳግም የጦርነት ነጋሪት መጎሰም ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡
በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት የተመሰረተውን የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በመገረሰስ፣ ኢ-ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ያነገበው ህወሃት በሚቆጣጠራቸው መገናኛ ብዙሃን የጦርነት ቀረርቶና ሕዝብን ከሕዝብ የሚያጋጩ የጥላቻ ንግግሮችን እያሰራጨ ይገኛል፡፡
በትግራይ ሕዝብ ላይ የአፈና ቀንበር የጫነው የህወሃት ቡድን ከውጭ ኃይሎች ጋር የጦርነት ጥምረት በመመስረት ግጭት መጠንሰስ የዕለት ግብሩ ሆኖ ቀጥሏል፡፡
ህወሃት በፕሪቶሪያ ስምምነት የተገኘውን ሰላም የሚጥሱ የጥፋት እንቅስቃሴዎችን ሲያደርግ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ለትግራይ ሕዝብ ደህንነት ቅድሚያ በመስጠት ጉዳዩን በትዕግሥት በመያዝ ለዘላቂ ሰላም ያለውን ቁርጠኝነት በተግባር አረጋግጧል፡፡
በግጭትና በጦርነት የተጎዳውን የትግራይ ሕዝብ ሕይወት ለመታደግ የኢትዮጵያ መንግሥት ተደጋጋሚ የሰላም ጥሪዎችንም ሲያደርግ ቆይቷል፡፡
በሥርዓተ-አልበኝነት ክልሉን የተቆጣጠረው ሕገወጡ የህወሃት ቡድን ግን ዛሬ የጦርነት አታሞ እየደለቀ በቀጠናው ሥጋት እየፈጠረ ይገኛል፡፡
የአዛውንቶቹ የጥፋት ቡድን በትግራይ የሚገኙ ወጣቶችንና ታዳጊዎችን በግዳጅና በማስፈራራት ወደ ጦር ካምፖች እያጋዘ ሌላ እልቂት ለመፍጠር እየተቅበዘበዘ ነው፡፡
ይህም ቡድኑ የትግራይ ሕዝብ እንደ ዋሻ የሚመሽግበት፣ መያዣ አድርጎ ለእኩይ የፖለቲካ ፍላጎቱ መጠቀሚያው እንጂ ደህንነቱ እንደማያሳስበው ማረጋገጫ ነው።
የቡድኑ የጥፋት እንቅስቃሴ ያንገሸገሻቸው ትግራዋይንም ተቃውሟቸውን እያሰሙ ይገኛሉ፡፡
የህወሃት ቡድን ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላት ውጭ ኃይሎች ጋር ጥምረት በመፍጠር፣ ከሰላም ይልቅ ጦርነትን መርጦ የትግራይ ወጣቶችን ለጦርነት መማገዱ ታሪክ ይቅር የማይለው ጥፋት ነው፡፡
በታደሰ ሽፈራው