ወደ ዋናው እና ወሳኙ የውይይት ምዕራፍ እየተሸጋገረ ያለው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር

AMN- ነሐሴ 1/2018 ዓ.ም

መሰረታዊ ልዩነቶችን እና አለመግባባቶችን ለመፍታት በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው ሀገራዊ ምክክር ወደ ዋናው እና ወሳኙ የውይይት ምዕራፍ እየተሸጋገረ ይገኛል፡፡

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሂደቱን በተቀመጠለት ዕቅድና የአሰራር ስነ-ዘዴ መሰረት እያከናወነ ሲሆን፤ በሂደቱ አብዛኛዎቹ ተሳታፊዎች መግባበባት በመፍጠር መስማማታቸውን እያረጋገጡ ነው፡፡

ተመካካሪዎች በባለሙያዎች የሚሰጡ ሳይንሳዊ ማብራሪያዎችን እያገኙ በልዩነቶች ላይ የጋራ መግባቢያ ነጥቦችን ለመፈለግ ጥረት እያደረጉም ይገኛል፡፡

ምክክሩ በኢትዮጵያ ለረጅም ዘመናት የነበሩ መሰረታዊ አለመግባባቶች እና ልዩነቶች በውይይት መፍትሄ እንዲያገኙ የሚያስችል ነው፡፡

ይሄም የፖለቲካ እና የማህበራዊ ጥያቄዎችን ለመፍታት ትልቅ እምርታ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።

ከዚህ ባለፈም በዜጎች መካከል የመተማመን መንፈስ እንዲፈጠር በማድረግ ዘላቂ ሰላም እና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲገነባ መሰረት የሚጥል እንዲሁም የሀገርን ራዕይም የሚያሳካ ነው፡፡

በዚህም ከተለያዩ አካባቢዎች የተመረጡ ተሳታፊዎች በሀገራዊ ምክክር ጉባዔው ተወያይተው የጋራ መግባባት ለመፍጠር ዋናው እና ወሳኙ ምዕራፍ ላይ ደርሰዋል፡፡

ተመካካሪዎች በውይይት መድረኮች ላይ የሚያጸድቋቸው ቃለ-ጉባዔዎችና የሚደርሱባቸው የመግባቢያ ሃሳቦች በቀጣይ ሀገራዊ መዋቅራዊ ለውጦች እና የሰላም ግንባታ ስራ ላይ እንደ ግብዓት የሚያገለግሉ ይሆናሉ።

ሀገራዊ የምክክር ጉባዔው ከባለ 10 አባላት 400 አነስተኛ ቡድኖች ጀምሮ ወደ ባለ 50 አባላት 80 ቡድኖች ከተሻገረ በኋላ ሰሞኑን ባለ 250 አባላት 16 ስልታዊ ቡድኖች ላይ መድረሱን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን መረጃ ያመላክታል፡፡

ሁሉም ስልታዊ ቡድኖች ተስማምተው በቃለ ጉባዔዎች ላይ ከተፈራረሙ የምክክር ሂደቱ ከስልታዊ ቡድን ወደ 500 አባላት ወዳሉት የሥራ ቡድን ይሸጋገራል፡፡

የሃገራዊ ምክክሩ ተመካካሪዎች የዳበረ እውቀትና ልምድ ያላቸው ሲሆኑ፤ ፖለቲከኞች፣ መምህራን፣ አርሶና አርብቶ አደሮች እንዲሁም ሴቶችና ሌሎች የማህበረሰብ ክፍሎች ይገኙበታል፡፡

የሻምበል ምህረት

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review