AMN – ግንቦት 3/2018 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ለሕጻናት የምትመች ከተማ ለሁሉም ትመቻለች ሲሉ ተናገሩ፡፡
ከንቲባ አዳነች ፤ ዛሬ የመጀመሪያውን ዓለም-አቀፍ የቀዳማይ ልጅነት ጉባኤ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትራችን አቶ ተመስገን ጥሩነህ በተገኙበት በውቧ ከተማችን አስጀምረናል ብለዋል።
አዲስ አበባ በቀዳማይ ልጅነት ልማት ዘርፍ የላቀ እና ተምሳሌት የሚሆን ተሞክሮ ያላት በመሆኗ፣ ይህን ዓለም-አቀፍ ጉባኤ ለማስተናገድ ተመራጭ አድርጓታል ነው ያሉት።
መንግስታችን በቀዳማይ ልጅነት ልማት ትርጉም ያለው ኢንቨስትመንት ማድረግ ምርጫ ሳይሆን የፓሊሲ ግዴታ አድርጎታል፡፡
በመሆኑም በከተማችን ከ2025 ጀምረን “አዲስ አበባን ህፃናትን ለማሳደግ ምርጧ የአፍሪካ ከተማ ለማድረግ አልመን “ከስድስት ዓመት በታች የሆኑ 1.3 ሚሊዮን ሕፃናት ተገቢ የጤና እንክብካቤ፣ ትምህርት እና ሁሉን-አቀፍ አገልግሎት ድጋፍ እንዲያገኙ ባለብዙ ዘርፍ ፕሮግራም ተግባራዊ እያደረግን እንገኛለን ብለዋል።
በዋናነትም በቀዳማይ ልጅነት ልማት ፕሮግራም ለ330,000 በኢኮኖሚ ተጋላጭ ቤተሰቦች ላይ ቅድሚያ ሰጥተን እየሰራን ነው ያሉት ከንቲባ አዳነች እስካሁን በመቶ ሺህ ለሚቆጠሩ ሕፃናት፣ ወላጆችና ቤተሰቦች የተቀናጀ ቀዳማይ ልጅነት ልማት አገልግሎት ተደራሽ አድርገናል፤ ይህም የመንግስታችን ለሰው-ተኮር ልማት ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያል ብለዋል።

በተለይም፣ ከ5,000 በላይ የወላጆች የአቅም ግንባታና ምክር ባለሙያዎችን አሰልጥነን ወደ ሥራ በማሰማራታችን አገልግሎቱን በቀላሉ ተደራሽ አድርጎታል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በ2015 በከተማችን 11 ብቻ የነበረዉ የህዝብ የሕፃናት ማቆያን በ2018 ወደ 1100 በማሳደግ የምግብ ፣ የህክምና፣ የስነ ልቦና የእንክብካቤ አገልግሎት በነፃ እየሰጠን ነው።
በተጨማሪም በ2015 በከተማችን 20 ብቻ የነበረዉን የልጆች መጫወቻ በ2018 ወደ 5000 በማሳደግ ልጆች ቦርቀዉ የሚያድጉበት አካባቢን መፍጠር ችለናል ብለዋል።
ከንቲባ አዳነች ፤ እየሰራናቸው ባሉት ስራዎች በእድገት ወደ ኋላ የቀሩ ህጻናት መጠን በ2015 መርሃ ግብሩን ስንጀምር ከነበረበት 13% ወደ 10% ዝቅ ማድረግ የቻልን ሲሆን የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ዝግጅታቸውም ከነበረበት 49% ወደ 90% ከፍ ማድረግ ተችሏል ሲሉ ገልጸዋል።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ ፤ በጉባኤዉ ላይ አዲስ አበባ በዚህ ዘርፍ ያላትን ምርጥ ተሞክሮዎች አጋርታለች ያሉ ሲሆን እንግዶቻችን በአዲስ አበባ የሚኖራቸው ቆይታ የተሳካ እና የሀገራችንን እና የከተማችንን መስህቦች የሚጎበኙበት እንዲሆን እመኛለሁ ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል