በ56 ዓመት ግለሰብ ፊኛ ውስጥ የነበረ 1.3 ኪሎ ግራም ጠጠር በቀዶ ሕክምና ተወገደ

  • Post category:ጤና

AMN – ግንቦት 14/2018 ዓ.ም

በቻይና የ56 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ግለሰብ ፊኛ ውስጥ የተፈጠረ 1.3 ኪሎ ግራም የሚመዝን ግዙፍ ጠጠር በቀዶ ሕክምና እንደተወገደላቸው ተዘግቧል።

በምዕራብ ጓንግዶንግ ግዛት ሎንግታንግ ከተማ የሚኖሩት አርሶ አደር፣ ከሦስት ዓመታት በፊት ጀምሮ በተደጋጋሚ የመሽናት ፍላጎትና የሽንት መውጣት ችግር ቢያጋጥማቸውም፣ ምልክቶቹን ቀላል አድርገው በመመልከታቸው ወደ ሕክምና ተቋም ለመሄድ ፈቃደኛ አልነበሩም።

ይሁን እንጂ ምልክቶቹ እየባሱ እና ሕመሙ እየጠነከረ በመምጣቱ፣ በቤተሰቦቻቸው ግፊት ወደ ሆስፒታል ሄደው ምርመራ አድርገዋል።

በዚያም በፊኛቸው ውስጥ የሽንት ፍሰትን የሚከለክል እጅግ ግዙፍ ጠጠር እንዳለ ተነግሯቸዋል።

በጓንግዶንግ ሕክምና ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል የሽንትና ፍሳሽ ሕክምና ክፍል ምክትል ዋና ሐኪም ሊን ዩዋን እንዳሉት፣ ከታካሚው የተወገደው ጠጠር 10 ሴንቲሜትር ስፋት እና 13 ሴንቲሜትር ርዝመት ያለው ሲሆን፣ ክብደቱም 1.3 ኪሎ ግራም ይደርሳል።

እንደ ሐኪሞቹ ገለጻ፣ ጠጠሩ በፊኛው ግድግዳ ላይ ለረጅም ጊዜ በፈጠረው ጫና ምክንያት የታካሚውን ሕይወት ሊያሰጋ የሚችል ሁኔታ ላይ ደርሶ ነበር።

ሆስፒታሉ የተለያዩ የሕክምና ዘርፎች ባለሙያዎችን ያካተተ ቡድን በማደራጀት ቀዶ ሕክምናውን በማከናወን ጠጠሩን በተሳካ ሁኔታ ማስወገዱ ተገልጿል።

እንደ ዘገባው ከሆነ፣ 1.3 ኪሎ ግራም የሚመዝነው ይህ ጠጠር በዓለም ላይ ከተመዘገቡት የፊኛ ጠጠሮች ሁሉ ትልቁ ባይሆንም፣ በጓንግዶንግ ግዛት ውስጥ እስካሁን ከተመዘገቡት መካከል ትልቁ መሆኑን ሐኪሞቹ ገልጸዋል።

በታደሰ ሽፈራው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review