የኢቦላ ስጋትን ለመግታት በኢትዮጵያ ጥብቅ የድንበርና የላቦራቶሪ ቁጥጥር ተጀመረ

AMN – ግንቦት 17/2018 ዓ.ም

የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) በግንቦት 9 ቀን 2018 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና በዩጋንዳ በቡንዲቡግዮ የቫይረስ ዝርያ የሚቀሰቀስ የኢቦላ በሽታ መከሰቱን ይፋ ማድረጉን ተከትሎ፣ በኢትዮጵያ ከፍተኛ የጥንቃቄ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

በሁለቱ ሀገራት በአጠቃላይ ከ101 በላይ በላቦራቶሪ የተረጋገጡ ታማሚዎች የተመዘገቡ ሲሆን፣ ከ900 በላይ ተጠርጣሪዎች ደግሞ የሕክምና ክትትል እየተደረገላቸው መሆኑ ተገልጿል።

ከፍተኛ የስርጭት እና የሞት ምጣኔ ያለው ይህ ወረርሽኝ ከሰው ወደ ሰው በንክኪ በቀላሉ የሚተላለፍ ቢሆንም፣ እስካሁን በኢትዮጵያ ምንም ዓይነት በበሽታው የተጠረጠረ ወይም የተያዘ ሰው አለመኖሩ ተረጋግጧል።

ኢትዮጵያ ወረርሽኙ ከተከሰተባቸው ሀገራት ጋር ቀጥተኛ የየብስ ድንበር ባይኖራትም፣ የበሽታውን አደገኛነት ከግምት ውስጥ በማስገባት የጤና ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር ሰፊ የመከላከል ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል።

በዚሁ መሠረት በሁሉም ዓለም አቀፍ የየብስ ኬላዎች እና በአየር ማረፊያዎች ላይ ጥብቅ የልየታና የቅኝት ሥራዎች ተጠናክረው የቀጠሉ ሲሆን፤ ወረርሽኙ ቢከሰት በፍጥነት ምላሽ መስጠት እንዲቻል የሕክምና ተቋማትና የላቦራቶሪዎች የመመርመር አቅም እንዲያድግ መደረጉ ተመላክቷል።

በተጨማሪም ለበሽታው መከላከያና መቆጣጠሪያ የሚያስፈልጉ ልዩ ልዩ የሕክምና ቁሳቁሶችና መድኃኒቶች አስቀድመው እንዲዘጋጁ መደረጉን ከጤና ሚኒስትር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ሚኒስቴሩ ሕብረተሰቡ አስፈላጊውን የጥንቃቄ መረጃዎች እንዲከታተልና ጥርጣሬዎች ሲኖሩም በአቅራቢያው ለሚገኙ የጤና ተቋማት በአስቸኳይ እንዲያሳውቅ አሳስቧል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review