AMN – ግንቦት 21/2018 ዓ.ም

በአሁኑ ወቅት በሰው ልጅ ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ትኩረትን የሚሰርቁና ሃሳብን የሚበትኑ ነገሮች በዝተዋል።
በዚህ ፈታኝ ወቅት ቀልብን ሰብስቦ ስኬታማ ህይወትን ለመምራት ምን ማድረግ ይገባል በሚለዉ የጤና ጉዳይ ላይ ኤኤምኤን የንቃተ ህሊና ማበልጸግ አሰልጣኝ ከሆኑት አቶ ናትናኤል ፋንታ ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡
በምድራችን ላይ እጅግ ውስብስብ የሆኑ እንደ ሱፐር ኮምፒውተሮች ያሉ ማሽኖች አሉ። ሆኖም ግን ከማንኛውም ማሽን በላይ እጅግ ረቂቅና ውስብስብ የሆነው የሰው ልጅ አእምሮ (Brain) ነው።

“ማንኛውንም ማሽን ስንገዛ እንዴት መጠቀም እንዳለብን የሚነግር ‘ማኑዋል’ ወይም መመሪያ አብሮት ይገኛል።
የእኛ አእምሮ ግን ከሁሉም በላይ ውስብስብ ሆኖ ሳለ እንዴት እንደምንጠቀመው የሚነግር ማኑዋል የለንም የሚሉት አቶ ናትናኤል ፋንታ በትምህርት ቤቶች ውስጥ መምህራን ተማሪዎቻቸውን ሃሳባችሁን በትኩረት አድርጉ፣ ቀልባችሁን ሰብስቡ (አስታውሱ)፣ አትሰልቹ ይላሉ እንጂ እንዴት ትኩረት ማድረግ እንደሚቻል፣ እንዴት አእምሮን ከመሰልቸት መከላከል እንደሚቻል ግን አያስተምሩም ይላሉ።
በሰለጠነው አለም ግን ይህ “ማይንደፉልነስ” ወይም ቀልብን መሰብሰብ ትኩረት ተሰጥቶት የሚሰጥ ትምህርት ነው።
አለም በአሁኑ ወቅት የሚያስተምረን በሃሳብ መበተንን (Deep Unconsciousness) ነው። የምናስባቸው አብዛኛዎቹ ሃሳቦች ከዕለት ተዕለት ግባችንና ከአለማችን ጋር የማይገናኙ ናቸው።

አንድ ሰው በቀን ውስጥ ወደ 70 ሺህ የሚጠጉ ሃሳቦችን ያስባል፤ የሶሻል ሚዲያ አጠቃቀማችን ደግሞ ይህንን ይበልጥ ያባብሰዋል ይላሉ።
የትኩረት ማጣት የሚያስከትላቸው ጉዳቶች
እንደ አቶ ናትናኤል ገለጻ፣ ሰዎች ቀልባቸውን መሰብሰብ ባለመቻላቸው ምክንያት ከሚፈጠሩት ችግሮች መካከል፣ ተማሪዎች ቀልባቸውን ሰብስበው ማንበብ አይችሉም።
ማንኛውም አይነት ስልጠና ቢሰጥ የሚፈለገው ለውጥ አይመጣም፤ ምክንያቱም ስልጠናውን ቀልብ ሰብስቦ የሚከታተል አእምሮ ስለማይኖር። የማዳመጥ ችሎታ በከፍተኛ ደረጃ ይቀንሳል ጥራት ያለው ስራ የመስራት ብቃት ይወርዳል።
ቀልብ የመሰብሰብ ትምህርት ጥቅሞች

ይህ የቀልብ መሰብሰብ ትምህርት ከኬጂ ጀምሮ እስከ ዩኒቨርሲቲ አልፎም እስከ ፓርላማም ድረስ ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ ሊሰጥ ይገባል ያሉት አሰልጣኙ፤ ይህ ከተደረገ፣ ከሱስ የጸዳ ትውልድ (Addiction-free Generation) መፍጠር ይቻላል፣የማስታወስ፣ የመማር እና የማጥናት ብቃቱ ከፍተኛ የሆነ ትውልድ ይገነባል ብለዋል፡፡
በአመክንዮ የሚያስብ (Rational Thinker) ማህበረሰብ ይፈጠራል ከሌላው አለም ጋር እውቀቱና የማሰብ አቅሙ እኩል የሆነ ትውልድ ይፈራል።
መፍትሄው
የአእምሮን አሰራር፣ ሃሳብ እንዴት እንደሚፈጠር እና ስሜትን እንዴት ማኔጅ ማድረግ እንደምንችል በጥልቀት ለመረዳት ወደ 16 ሰዓታት አካባቢ የሚፈጅ ስልጠና እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡
ለጊዜው ግን መጠቀም የምንችለው ቀላሉ መፍትሄ ትንፋሽን ማዳመጥ፣ ለምሳሌ፦ አሁንም ንግግር እያደረጉ ወይም ስራ እየሰሩ ከጀርባ እየተነፈሱ መሆናቸውን ማወቅ።
ይህንን ሲያደርጉ ሙሉ ለሙሉ አሁን ባሉበት ሰዓት (Present Moment) ላይ ይገኛሉ፤ ራሳቸውን ግራውንድ ያደርጋሉ ይላሉ።
ይህ ቀላል ልምምድ ብቻውን ትልቅ ለውጥ ያመጣል የሚሉት አቶ ናትናኤል፤ ነገር ግን ዘላቂነት ያለው ውጤት ለማግኘት መለማመድና ስነምግባር ይጠይቃል ብለዋል።
በፍሬሕይወት ብርሃኑ