ሜድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ 7 ዓይነት በጉሉኮስ መልክ የሚሰጡ የተለያዩ የህፃናት መድሀኒቶችን አስተዋወቀ

AMN – ሐምሌ 7/2018 ዓ.ም

ምርቶቹ በ100 ሚሊ ሊትር የተዘጋጁ ሲሆን፣ የክሊኒካል ክፍተትን ከመሙላታቸውም በተጨማሪ የውጭ ምንዛሬ በማዳን ረገድ ከፍተኛ አስተዋዕፆ እንዳላቸው ተመላክቷል።

በመድረኩ የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ፍሬህይወት አበበ፣ ኢትዮጵያ ከሶስት ዓመታት በፊት መድሃኒቶችን በሀገር ውስጥ የማምረት አቅሟ 8 በመቶ ብቻ የነበረ መሆኑን አስታውሰዋል።

አሁን ላይ ግን 44 በመቶ የሚሆኑ መድሀኒቶችን ሙሉ በሙሉ በሀገር ውስጥ ማምረት መቻሉን ገልፀዋል።

ይህም መንግስት ለጤናው ዘርፍ የሰጠውን ትኩረት አመላካች እና ኢትዮጵያ ከመድሃኒት እና ከህክምና ግብዓት ጋር በተገናኘ ከጥገኝነት ተላቃ ራሷን እንድትችል ትልቅ አቅም የሚፈጥር መሆኑን ተናግረዋል።

በሜድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ አማካኝነት በዛሬው ዕለት የተዋወቁት 7 ዓይነት በጉሉኮስ መልክ የሚሰጡ (አይቪ ፍሉድ) የህፃናት መድሀኒቶች ናቸው፡፡

በሜድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ የፋርማኪዩር ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን ገብረአማኑኤል፣ ቀደም ሲል አብዛኛውን መድሃኒት ከውጭ ለማስገባት ይወጣ የነበረውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የሚቀንስ እንደሆነ ገልጸዋል።

የመድሃኒት አቅርቦት ዋስትናን በማረጋገጥ ዓለም አቀፍ የአቅርቦት ሰንሰለት መስተጓጎል በሚኖርበት ጊዜ እንኳን መሠረታዊ መድኃኒቶች በሀገር ውስጥ በቀላሉና በወቅቱ እንዲገኙ ትልቅ አቅም የሚፈጥር መሆኑንም አብራርተዋል።

በሀገር ውስጥ የሚገነቡ የፋርማሲዩቲካል ፋብሪካዎች ለዜጎች ሰፊ የሥራ ዕድልና የቴክኖሎጂ ሽግግር የሚፈጥሩ መሆናቸውም ተመላክቷል።

በትባረክ ኢሳያስ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review