AMN-ሀምሌ 05/2018 ዓ.ም
አዲስ አበባን የጤና ቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ በተያዘው ራዕይ መሠረት፣ከተማ አስተዳደሩ ባለፉት አምስት ዓመታት በጤናው ዘርፍ መጠነ ሰፊ የመሠረተ ልማት እና የአገልግሎት ጥራት ማሻሻያዎችን ማከናወኑን አስታውቋል።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ የአስተዳደራቸውን የ2018 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ለከተማዉ ምክር ቤት ባቀረቡበት ወቅት እንደገለጹት ፤ አዲስ አበባ በጤናው ዘርፍ ታሪካዊ ለውጥ በማስመዝገብ የአገልግሎት አቅሟን በእጥፍ አሳድጋለች ብለዋል።
በዚህም መሠረት የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ከእጥፍ በላይ በማሳደግ፣ የእናቶችና የጨቅላ ህፃናት ሞት ምጣኔን ከዓለም ጤና ድርጅት እና ከሀገር አቀፍ ደረጃዎች በላይ በመቀነስ ረገድ ስኬታማ ውጤቶች ተመዝግበዋል ብለዋል።

የጤና ተቋማትን የአልጋ ቁጥር ከነበረበት 1 ሺህ 384 ወደ 4 ሺህ 195 ከፍ በማድረግ በዘርፉ ባለፉት መቶ ዓመታት ከተመዘገበው እድገት በእጥፍ የሚበልጥ አፈጻጸም መመዝገቡ ተገልጿል።
በአበበች ጎበና፣ ላፍቶ፣ ኮልፌ እና ገላን ድንገተኛ ሆስፒታሎች ግንባታ እና በዳግማዊ ሚኒሊክና ዘውዲቱ ሆስፒታሎች ላይ በተደረጉ ማስፋፊያዎች ዘመናዊ የህክምና አገልግሎቶች ተደራሽ ሆነዋልም ብለዋል።
በተጨማሪም የህክምና መሳሪያዎችን ከማሟላት ባሻገር፣ የአምቡላንስ አገልግሎትን ከ30 ወደ 109 በማሳደግ ድንገተኛ የህክምና አገልግሎት ተደራሽነት ተጠናክሯል ብለዋል።
የከተማ አስተዳደሩ በማህበራዊ ፍትህ አፈጻጸም ረገድ 2 ነጥብ 7 ሚሊዮን ነዋሪዎችን በጤና መድህን በማቀፍ በየአመቱ ከ1.2 ቢሊዮን ብር በላይ ድጎማ እያደረገ ይገኛል።
በተለይም በዳግማዊ ሚኒሊክ እና ዘውዲቱ ሆስፒታሎች የኩላሊት እጥበት የሚያስፈልጋቸው ታካሚዎች በነጻ አገልግሎት እንዲያገኙ በዓመት እስከ 100 ሚሊዮን ብር እየተደጎመ መሆኑ ከንቲባዋ አክለዋል።

ከተማዋን ለህጻናት ምቹ ለማድረግ የተጀመረው የቀዳማይ ልጅነት ልማት ፕሮግራምም ስኬታማ አፈጻጸም እያሳየ ሲሆን፣ በ5 ሺህ ሰራተኞች አማካኝነት በየቤቱ የጤና ምክር አገልግሎት የመስጠት ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል።
አስተዳደሩ የጤና ፖሊሲውን በተግባር ለማዋል ፅዱ፣ አረንጓዴ እና ለስፖርት እንቅስቃሴዎች አመቺ የሆኑ አካባቢዎችን በመፍጠር የነዋሪዎችን ደህንነት እየጠበቀ መሆኑንም አንስተዋል።
በሚካኤል ህሩይ