AMN- ሐምሌ 7/2018 ዓ.ም

በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ 48 ሀገራት የተሳተፉበት 23ኛው የዓለም ዋንጫ ሊጠናቀቅ የአራት ጨዋታዎች እድሜ ብቻ ቀርቶታል።
ሦስት የአውሮፓ ሀገራትን እና አንድ የደቡብ አሜሪካ ሀገርን ብቻ ያስቀረው ውድድሩ ዛሬ ግማሸ ፍፃሜውን ይጀምራል። የመጀመሪያው የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታ በፈረንሳይ እና ስፔን መካከል ዛሬ ይከናወናል።
ውድድሩ ከመጀመሩ በፊት የበርካታ ደጋፊዎች ፣ ተንታኞች ሌሎችም ግምታቸው ፈረንሳይ አልያም ስፔን የዋንጫ አሸናፊ ይሆናሉ የሚል ነበር። እነዚህ ሁለት ሀገራት እንደተጠበቁት ረዥም ርቀት ተጉዘው ግማሽ ፍጣሜ ደርሰዋል። አሁን ጥያቄው ማን የፍፃሜ ተፋላሚ ይሆናል? የሚል ነው።
ፈረንሳይ በውድድሩ ታሪክ ከስፔን የተሻለ የዳበረ ታሪክ አላት። የዛሬ ጨዋታ ለፈረንሳይ በዓለም ዋንጫው ስምንተኛ የግማሽ ፍፃሜ ፍልሚያዋ ነው። በዓለም ዋንጫው ግማሽ ፍፃሜ በመድረስ ፈረንሳይ የምትበልጠው 12 ጊዜ ያለፈችው ጀርመን ብቻ ናት።
ፈረንሳይ የግማሽ ፍፃሜ ከደረሰችባቸው አራት የመጨረሻ አጋጣሚዎች በሁሉም ድል ቀንቷት ወደ ፍፃሜ ተሸጋግራለች። ዛሬ ካሸነፈች ለሦስት ተከታታይ ጊዜ ፍፃሜ በመድረስ ጀርመን እና ብራዚል የሰሩትን ታሪክ ትጋራለች።
ፈረንሳይ በዛሬው ጨዋታ በማጥቃት ሃይሏ ትመካለች። በተለይ ኪሊያን ምባፔ እና ኡስማን ዴምቤሌ ጥምረት ተከላካዮችን የሚያርድ ነው። ኪሊያን ምባፔ ስምንት ፣ ኡስማን ዴምቤሌ ደግሞ አምስት ግቦችን አስመዝግበዋል። ሁለቱ ተጫዋቾች አንዱ ለሌላው በጋራ 19 የግብ እድሎችን ፈጥረዋል።
ስፔን በመጀመሪያ ጨዋታዋ ከኬፕ ቨርድ ጋር አቻ ተለያይታ ወቀሳ ቢበዛባትም ጉዞዋን አሳምራ በታሪኳ ለሁለተኛ ጊዜ ግማሽ ፍፃሜ ደርሳለች። ከዚህ ቀደም ደቡብ አፍሪካ ባሰናዳችው የ2010 የዓለም ዋንጫ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ግማሽ ፍጣሜ መድረሷ ይታወሳል።
ስፔን በታላላቅ ውድድሮች ላይ ያላት ክብረወሰን የትኛውም ተጋጣሚ አክብሮት እንዲሰጣት ያስገድዳል። ከ2018ቱ የዓለም ዋንጫ በኋላ በታላላቅ ውድድሮች ላይ ካደረገቻቸው 27 ጨዋታዎች አንድ ብቻ ነው የተሸነፈችው። በእነዚህ ጨዋታዎች አምስት ግብ ብቻ ነው የተቀቆጠረባት።
ስፔንን በርካቶች በኳስ ቁጥጥሯ እና በርካታ ግብ በማስቇጠር ቢያቋትም የተከላካይ ክፍሏም ትልቅ ቦታ ይሰጠዋል። በዘንድሮ የዓለም ዋንጫ ሩብ ፍፃሜ ላይ ቤልጂየምን 2ለ1 ሲያሸንፉ ነው ለመጀመሪያ ጊዜ ግብ የተቆጠረባቸው።
እስካሁን በውድድሩ የገጠሟቸው ብሔራዊ ቡድኖች ግን በፈረንሳይ ደረጃ የላቀ የፊት መስመር የያዙ አልነበሩም። የስፔን ተከላካይ ክፍል የሚፈተንበት ትክክለኛው ጨዋታ ዛሬ ይመስላል።
ምሽት 4፡00 ከ70 ሺ በላይ ተመልካቾችን መያዝ በሚችለው ዳላስ ስታዲየም የሚከናወነውን እጅግ አጓጊ ጨዋታ ማን ያሸንፋል? ፈረንሳይ ወይስ ስፔን ፤ ኪሊያን ምባፔ ወይስ ላሚን ያማል፦ ማን ወደ ፍፃሜ ያልፋል? የኤልሳልቫዶር ዜግነት ያላቸው ኢቫን በርተን በዋና ዳኝነት የሚመሩት ጨዋታ ምላሾቹን ይሰጠናል።
በሸዋንግዛው ግርማ