የመራጮች ጠንካራ ተሳትፎ ለምርጫው ስኬታማነት ወሳኝ ሚና ተጫውቷል

AMN- ግንቦት 25/2018 ዓ.ም

ለሰባተኛው የኢትዮጵያ ጠቅላላ ምርጫ ስኬታማነት የመራጩ ሕዝብ ጠንካራ ተሳትፎ ወሳኝ ሚና መጫወቱን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ሀይሉ ገለፁ።
ሰብሳቢዋ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም በተካሄደው ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ አጠቃላይ ሂደት ዙሪያ ለመገናኛ ብዙሃን ዝርዝር መግለጫ ሰጥተዋል።

በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፣ በርካታ የፖለቲካ ፓርቲና የግል ዕጩዎች የተወዳደሩበት ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በስኬት ተጠናቋል።

ለዚህ ስኬት ደግሞ ቦርዱ በቅድመ ምርጫ ሂደት ያከናወናቸው ዘርፈ ብዙና የተቀናጁ ተግባራት ለሂደቱ መቃናት ጠንካራ መሠረት መሆናቸውን አብራርተዋል።

በምርጫው ዕለት የታየው የሕዝብ ተነሳሽነት እጅግ ከፍተኛ እንደነበር የገለጹት ሰብሳቢዋ፤ መራጩ ሕዝብ የአየር ፀባይ ሳይበግረው በጽናት በመቋቋም ያሳየውን ተሳትፎ አድንቀዋል።

መራጩ ሕዝብ ከማለዳው 12፡00 ሰዓት ጀምሮ ድምፁን ሲሰጥ መዋሉን ገልጸው፤ አዲስ አበባን ጨምሮ ረጃጅም ሰልፍ የነበረባቸውን የምርጫ ጣቢያዎች እስከ እኩለ ሌሊቱ 6፡00 ሰዓት በማራዘም መራጮች ድምፅ እንዲሰጡ መደረጉን አውስተዋል።

መራጩ ሕዝብ ምሽቱ ሳያሳስበው በታላቅ ትዕግሥት ተሰልፎ ዴሞክራሲያዊ መብቱን መጠቀሙን ገልጸው፤ ይህ ጠንካራ ተሳትፎም ምርጫው ስኬታማ እንዲሆን ወሳኝ ሚና ተጫውቷል ብለዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review