የሸገር ከተማ ሁለተኛው ዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት ኤክስፖ ተከፈተ

You are currently viewing የሸገር ከተማ ሁለተኛው ዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት ኤክስፖ ተከፈተ

AMN-ሰኔ 26/2018 ዓ.ም

የሸገር ከተማ ሁለተኛው ዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት ኤክስፖ “ዕድል ለሁሉም” በሚል መሪ ቃል በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት በይፋ ተከፍቷል።

የኤክስፖው ዓላማ የሸገር ከተማን የኢኮኖሚ ማዕከል ለማድረግ፣ በቴክኖሎጂ የተደገፈ የአገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓት ለመዘርጋት ፣ የከተማዋን የኢንቨስትመንት አቅም ለማጠናከርና ቀደም ሲል በዘርፉ የነበሩ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመቅረፍ ከተማዋን ማስተዋወቅ እንደሆነ ተገልጿል።

የጨፌ ኦሮሚያ አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ሳዓዳ አብዱራህማን ፣ ሸገር ከተማ አዲስ የኢኮኖሚና የቴክኖሎጂ ማዕከል ሆና የተገነባች ከተማ መሆኗን ገልጸዋል።

ከተማዋ የብልጽግና እሳቤን አንግባ የተመሠረተችና ሰፊ የኢንቨስትመንት ዕድል ያላት መሆኑንም አንስተዋል።

በአሁኑ ወቅት እየተስፋፋ ያለው ኢንቨስትመንት አርሶ አደሩን የሚያፈናቅል ሳይሆን የሚያቅፍና በኢኮኖሚው ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ እንዲኖራቸው የሚያደርግ መሆኑን አስረድተዋል።

ይህ ኤክስፖም የሸገር ከተማን የኢንቨስትመንት እምቅ አቅም በማስተዋወቅ የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶችን ለመሳብ እና የገበያ ትስስር ለመፍጠር ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት ገልጸዋል።

በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ምክትል ፕሬዚዳንት ማዕረግ የሸገር ከተማ ከንቲባ ተሾመ አዱኛ(ዶ/ር) በበኩላቸው ሸገር ከተማ አዲስ ኢኮኖሚ በመፍጠር የሕዝቡን ጥያቄ ለመመለስ የተገነባች ከተማ ናት ብለዋል።

ለኢንቨስትመንት ዘርፉ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ባለው ሥራም ትልቅ ኢኮኖሚ እየተገነባ መሆኑን ተናግረዋል።

እስከ ሰኔ 28/2018 ዓ.ም ድረስ እንደሚቆይ የተገለጸው ይህ ኤክስፖ ፣ የምርቶች ግዢና ሽያጭ የሚካሄድበት፣ የኢንቨስትመንት ድርጅቶች ምርቶቻቸውን የሚያስተዋውቁበት፣ ልምድ የሚለዋወጡበትና የገበያ ትስስር የሚሰፋበት ይሆናል ተብሏል።

በመሀመድኑር ዓሊ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review