AMN – ሰኔ 02/2018 ዓ.ም
ማር ተፈጥሮ ይዘት ያለውና ለብዙ በሽታዎች ፈውስ እንደሆነ ቢታወቅም፣ ለሕፃናት በሚሰጥበት ጊዜ ግን ከፍተኛ ጥንቃቄ እንደሚያስፈልግ የሕፃናትና እናቶች ሕክምና ስፔሻሊስት ያስጠነቅቃሉ።
በተለይም ከአንድ ዓመት በታች ለሆኑ ሕፃናት ማር መስጠት ከባድ አደጋ እንዳለው ባለሙያው በዝርዝር ያብራራሉ።
በአበበች ጎበና ሆስፒታል የሕፃናትና እናቶች ሕክምና ስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ር ኤርሚያስ ጌታቸው ለኤ ኤም ን እንደገለጹት፣ በማር ውስጥ ክሎስትሪዲየም ቦቱሊነም የተሰኘ ባክቴሪያ ይገኛል።
ይህ ባክቴሪያ በአዋቂዎች ላይ ምንም ዓይነት የጤና ችግር ባይፈጥርም፣ ከአንድ ዓመት በታች ለሆኑ ሕፃናት ግን ለሕይወት አስጊ የሆነ አደጋ አለው።

ለዚህም ዋናው ምክንያት የሕፃናቱ በሽታ የመከላከል አቅም ገና በሚገባ ያልዳበረ በመሆኑና በጨጓራቸው ውስጥ ባክቴሪያውን ተከላክሎ የሚያጠፋ በቂ አሲድ ስለማይመነጭ ነው።
ይህ ባክቴሪያ አንዴ ወደ ሕፃኑ ሰውነት ከገባ በኋላ መርዛማ ንጥረ ነገር በማመንጨት ቀጥታ ወደ ነርቭ ሥርዓት ይዛመታል።
በዚህም ሳቢያ ሙሉ ሰውነትን የማዝለፍለፍ ወይም የመንቀሳቀስ አቅም የማሳጣት፣ ዓይንን ለመግለጥ የመቸገር፣ ጡት የመጥባት አቅም የማጣት እንዲሁም ጭንቅላትን ቀና አድርጎ መሸከም አለመቻል ምልክቶች ይታዩበታል።

ችግሩ እየባሰ ሲሄድም የመተንፈሻ አካላትን ሥራ ሙሉ በሙሉ በማሰናከል፣ ሕፃኑ በራሱ መተንፈስ አቅቶት በሕክምና ማሽን እስከ መታገዝ ሊደርስ እንደሚችል ዶ/ር ኤርሚያስ ያስረዳሉ።
ዶ/ር ኤርሚያስ አክለው እንደገለጹት፣ ሕፃናት ከአንድ ዓመት በላይ ሲሆናቸው ግን በሽታ የመከላከል አቅማቸው ስለሚጠነክርና ጨጓራቸውም ባክቴሪያውን የሚያመክን በቂ አሲድ ማመንጨት ስለሚጀምር ማር ቢመገቡ እንኳ ምንም ዓይነት የጤና ችግር አይገጥማቸውም።
ከዚህም ባሻገር፣ ዕድሜያቸው ከአንድ ዓመት በላይ ለሆኑ ሕፃናት ከጉንፋን ጋር ተያይዞ ለሚከሰት ቀላል ሳል፣ ጠዋት ጠዋት ሁለት የሻይ ማንኪያ ማር መስጠት ሳሉን በእጅጉ እንደሚቀንሰውና በሂደትም ሙሉ በሙሉ እንደሚያጠፋው ባለሙያው ይመክራሉ።

በሌላ በኩል፣ በማኅበረሰቡ ውስጥ ሕፃናት ማር ቢበሉ አንደበታቸው ይኮላተፋል ወይም ንግግራቸው ይዘገያል የሚል በሰፊው የሚነገር የተሳሳተ አመለካከት እንዳለ የጠቀሱት ዶ/ር ኤርሚያስ፣ ይህ አባባል ሙሉ በሙሉ ከሳይንሳዊ እውነት የራቀ መሆኑን ይናገራሉ።
ማር የመመገብ እና የንግግር ችሎታ ማደግ ምንም ዓይነት ቀጥተኛም ሆነ ተዘዋዋሪ ግንኙነት የላቸውም። በመሆኑም ወላጆች የሕፃናትን የመናገር መቸገር ወይም መኮላተፍ ካስተዋሉ ወደ ሕክምና ተቋም በመሄድ ተገቢውን የሕክምና ምርመራና ምክር ሊያገኙ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በፍሬሕይወት ብርሃኑ