ስብሰባችንን ተከትሎ እጅግ ዘመናዊና ፈጣን የቴክኖሎጂ ግብዓቶችን በመጠቀም የተገነቡ ቤቶችን የሚያሳይ የግንባታ ሳይት ጎብኝተናል – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

AMN- ሰኔ 2/2018 ዓ.ም

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ስብሰባችንን ተከትሎ፣ እጅግ ዘመናዊና ፈጣን የቴክኖሎጂ ግብዓቶችን በመጠቀም የተገነቡ ቤቶችን የሚያሳይ የግንባታ ሳይት ጎብኝተናል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በማህራዊ ትስስር ገጻቸው በሰፈሩት መልዕክት ፤ በዚህ ሳይት ሦስት የላቁ የግንባታ ዘዴዎች በጥምረት ጥቅም ላይ ውለዋል፤ የ3ዲ ህትመት(3D printing)፣ የቅድመ-ዝግጅት ቀላል የአረብ ብረት ግንባታ እና የኮንቴይነር መኖሪያ ቤቶች ናቸው ብለዋል።

እያንዳንዳቸው ግንባታዎች ትክክለኛውን ቴክኖሎጂ ስንጠቀም ፍጥነት እና ጥራት እርስ በእርስ የማይጋጩ መሆናቸውን ያረጋገጡ ሲሆን፤ ጥራታቸውን የጠበቁ መኖሪያ ቤቶችን ከወራትና ከዓመታት ይልቅ በጥቂት ቀናት እና ሳምንታት ውስጥ ሰርቶ ማጠናቀቅ እንደሚቻል የታየበት ህያው ምስክር ናቸው ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

ይህ አይነቱ የላቀ ፈጠራ በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል በቀላሉ ሊተገበር፣ ሊደገም እና ሊስፋፋ የሚችል በመሆኑ የሀገራችንን የቤት ልማት ፕሮግራም አቅጣጫ በከፍተኛ ደረጃ የመቀየር ኃይል አለውም ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፤ ቴክኖሎጂን ከሀገራዊ ርዕያችን ጋር አጣምረናል፤ መሰል በተግባር የተገለጡ ስራዎቻችን ደግሞ ለሀገር የሚገባውን ፈጣን እድገት እውን ለማድረግ በትክክለኛው አቅጣጫ ላይ በቁርጠኝነት እየተጓዝን መሆናችንን በተግባር አሳይቷል ሲሉ ገልጸዋል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review