AMN – ጥቅምት 9/2019 ዓ.ም
ኢትዮጵያ በስፔስ ሳይንስና ጂኦስፓሻል ዘርፍ በግንባር ቀደምትነት እየሰራች መሆኑን በተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን የጂኦ-ስፓሻል መረጃ አስተዳደር ክፍል ኃላፊ አንድሬ ኖንጉዌማ ገለጹ።
የተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ዓለም አቀፍ የጂኦስፓሻል መረጃ አስተዳደር 12ኛ ጉባዔ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።
ጉባዔው ከዛሬ ጥቅምት 9 ቀን 2019ዓ.ም ጀምሮ ለአምስት ቀናት የሚካሄድ ሲሆን የጂኦስፓሻል መሪዎችን፣ ፖሊሲ አውጪዎችንና የልማት አጋሮችን የሚሳተፉበት ይሆናል።
ጉባዔው በአፍሪካ የጂኦስፓሻል መረጃ አስተዳደር ዘላቂ የፋይናንስ አቅርቦትና ፈጠራ ላይ የሚመክር ሲሆን በዛሬው ዕለት የቅድመ ጉባዔ መድረክ ተካሂዷል።
በዚህ ወቅት በተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን የጂኦ-ስፓሻል መረጃ አስተዳደር ክፍል ኃላፊ አንድሬ ኖንጉዌማ እንዳሉት ጉባዔው አባል ሀገራት ያላቸውን ትብብር ለማጠናከር በጋራ የሚመካከሩበት መድረክ የሚፈጥር ነው።
የጂኦስፓሻል መረጃ እንደ መንገድ፣ ግድብና ትምህርት ቤት ግንባታ አስፈላጊ የሆነ መሠረተ ልማት ከመሆኑም በላይ ለእያንዳንዱ የመሠረተ ልማት ግንባታ የጂኦስፓሻል መረጃ ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ ብሔራዊ የስፔስ አቅም በማልማት ግንባር ቀደምት ሆና በዘርፉ እየሰራች መሆኑን ጠቅሰው የመሬት ምልከታ ሳተላይትን ማምጠቋን አንስተዋል።
ለአባል አገራት፣ ለፖሊሲ አውጪዎችና ለውሳኔ ሰጪዎች የጂኦስፓሻል መረጃን እንደሌሎች መሠረተ ልማቶች ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩበት እንደሚገባ ገልጸዋል።
ትክክለኛ መረጃ ለዕቅድ ዝግጅት፣ ለልማት ስራዎችና ክትትል ለማድረግ ወሳኝ በመሆኑ ይህን በመገንዘብ መስራት ይጠይቃል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።