የኢትዮጵያ የውሃና ኢነርጂ ልማት በፍትሐዊና ምክንያታዊ ትብብር ላይ የተመሰረተ ነው

You are currently viewing የኢትዮጵያ የውሃና ኢነርጂ ልማት በፍትሐዊና ምክንያታዊ ትብብር ላይ የተመሰረተ ነው

AMN – ጥቅምት 16/2019 ዓ.ም

የኢትዮጵያ ድንበር ተሻጋሪ የውሃ ሀብቶች ልማት በፍትሐዊና ምክንያታዊ የትብብር መንፈስ ላይ የተመሰረተ መሆኑ ተገለጸ።

3ኛው የኢትዮጵያ የውሃና ኢነርጂ ሳምንት «ለውሃና ኢነርጂ ዋስትና የተጠበቀለት የወደፊት ሁኔታ፤ ሳይንሳዊ መሠረት ያላቸውን ፖሊሲዎችና አጋርነቶች ማሳደግ» በሚል መሪ ሀሳብ መካሄድ ጀምሯል።

በአዲስ አበባ ሳይንስ ሙዚየም በይፋ በተከፈተው መርሃ ግብር ላይ የሀገራት አምባሳደሮች፣ ተመራማሪዎች፣ ፖሊሲ አውጪዎችና ባለድርሻ አካላት ታድመዋል።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ሃብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) በተወካያቸው በኩል እንደገለጹት፤ የውሃና ኢነርጂ ልማት የአካባቢ ጥበቃን በማጎልበት ለሁለንተናዊ ሀገራዊ ዕድገት መሠረት ናቸው።

ሁለቱ መሠረታዊ ሀብቶች የግብርና ምርታማነትን በማሳለጥ ለምግብ ዋስትና፣ ለሕዝብ ጤና፣ ለኢንዱስትሪ ዕድገት፣ ለሥራ ዕድል ፈጠራ እና ለአካባቢ ዘላቂ ደኅንነት ወሳኝ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያን የውሃና ታዳሽ ኢነርጂ አቅም በሳይንሳዊ ጥናትና በተረጋገጠ የፖሊሲ መረጃ በማስደገፍ፣ ተቋማዊ አቅምን ማጠናከር የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎች ጥቅም ላይ እየዋሉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ለአብነትም የኃይል አቅርቦት፣ የውሃና ንጽህና አጠባበቅ ሥርዓት፣ የመስኖ ልማትና የውሃ አጠቃቀም፣ እንዲሁም የገጸና ከርሰ ምድር የውሃ ሀብቶች ልማት ትኩረት የተሰጣቸው መሆኑን አንስተዋል።

ከዚህ ባለፈም የኢትዮጵያን የውሃና ኢነርጂ መሠረተ ልማቶች በማስፋት ዜጎች የሚፈልጉትን የአገልግሎት አቅርቦት ፍላጎት ለማሟላት ሰፋፊ ሥራዎች እየሠሩ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያን የውሃና ኢነርጂ ልማት ለማፋጠን የመንግሥት፣ የከፍተኛ ትምህርትና ምርምር ተቋማት፣ የግሉ ዘርፍ እና የልማት አጋሮች መካከል የሚደረገውን ትብብር ማጠናከር አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበዋል።

ድንበር ተሻጋሪ የውሃ ሀብቶችን ፍትሐዊና ምክንያታዊ አጠቃቀም በማረጋገጥ፣ በትብብርና በመተማመን ላይ በተመሠረተ አካሄድ የጋራ ብልጽግናን ለማምጣት እየተጋች መሆኑን ያነሱት ሚኒስትሩ፤ የኢትዮጵያ የውሃና ኢነርጂ ልማት በትብብር፣ በፍትሐዊና ምክንያታዊ የሀብት አጠቃቀም እንዲሁም የጋራ ብልጽግናን በሚያረጋግጥ አጋርነት ላይ የተመሰረተ መሆኑን አስረድተዋል።

መድረኩ በሳይንሳዊ መረጃ የተደገፉ ፖሊሲዎችንና ትብብርን በማጠናከር፣ ለዘላቂ የውሃና ኢነርጂ ዋስትና የሚያግዙ ሀሳቦችን፣ ልምዶችንና መፍትሔዎችን ለመለዋወጥ የሚያስችል መሆኑን ኢዜአ ዘግቧል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review