AMN – ሰኔ 3/2018 ዓ.ም
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአገር አቀፍ ደረጃ እያከናወነ ባለው የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከፍተኛና ንቁ ተሳትፎ እያደረገ መሆኑን የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ ገለጹ።
ዋና ኮሚሽነሩ ኮሚሽኑ እስካሁን ያከናወናቸውን ተግባራት፣ ያጋጠሙ ተግዳሮቶች እና የተወሰዱ የመፍትሄ እርምጃዎችን እንዲሁም የቀጣይ ዕቅዶችን አስመልክቶ ዝርዝር ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደቱ ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የተገኘው ተሳትፎ አበረታች መሆኑን የገለጹት ፕሮፌሰር መስፍን፤ በተለይም በክልሎች የሚገኙ የሃይማኖት ተቋማት፣ ምሁራን፣ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች፣ የሠራተኛ ማህበራት፣ አካል ጉዳተኞች እንዲሁም ዓለም አቀፍ ማህበረሰቡ በሂደቱ ውስጥ በንቃት በመሳተፍ ግብዓቶችን እያቀረቡ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

ኮሚሽኑ አብዛኞቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች በምክክር ሂደቱ ውጤታማ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር ላይ እንደሚገኝ የገለጹት ዋና ኮሚሽነሩ ፣ የቀሩትን የፖለቲካ ፓርቲዎችም ወደ ምክክር ሂደቱ ለማምጣት ኮሚሽኑ ያላሰለሰ ጥረት እያደረገ መሆኑን አረጋግጠዋል።
በተጨማሪም ኮሚሽኑ በየአካባቢው የሚገኙ ታጣቂ ኃይሎች ወደ ሰላማዊ መንገድ እንዲመጡና አጀንዳዎቻቸውን በምክክር ሂደቱ ላይ እንዲያቀርቡ ለማስቻል ጥረት እያደረገ መሆኑን ፕሮፌሰር መስፍን ጠቅሰዋል።
በአሁኑ ወቅት ኮሚሽኑ የአገር አቀፍ እና የክልል የፖለቲካ ፓርቲዎችን የአጀንዳ ቀረጻ ግብዓቶች እየሰበሰበ የሚገኝ ሲሆን፣ የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ የሚካሄድበትን ትክክለኛ ቀን በቅርቡ ይፋ እንደሚያደርግ ይጠበቃል።
በ ንጉሱ በቃሉ