AMN – ሚያዝያ 12/2018 ዓ.ም
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት የተካሄደው የ100 ቀናት ግምገማ እና የዘጠኝ ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት፣ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ መሆኑን አመላክቷል።
የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) ባቀረቡት ሪፖርት፣ በአሁኑ ወቅት የኢኮኖሚ ዕድገቱ 9.2 በመቶ የደረሰ ሲሆን፣ በበጀት ዓመቱ ማብቂያ ላይም ወደ 10.2 በመቶ ከፍ ይላል ተብሎ ይጠበቃል።
ይህም ባለፉት ስምንት ዓመታት የተመዘገበውን የ7.5 በመቶ አማካይ ዕድገት በከፍተኛ ደረጃ የሚያሻሽል ነው። ይህ ውጤት የተመዘገበው መንግሥት የፋይናንስ ሥርዓቱን ለማጠናከር በወሰዳቸው ስር ነቀል እርምጃዎች መሆኑ ተገልጿል።
በተለይም የካፒታል ገበያ ልማት መጀመሩና በመንግሥትና በግል አጋርነት የተዘረጉ አዳዲስ የፋይናንስ አማራጮች ለኢኮኖሚ አስተዳደሩ መጠናከር ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ውጤታማ የዕዳ ሽግሽግ በማድረግ የሀገሪቱን የፋይናንስ ጫና ማቃለል መቻሉ ተመላክቷል። በሪፖርቱ ከተጠቀሱት አስደናቂ ስኬቶች መካከል የመንግሥት የልማት ድርጅቶች አፈጻጸም ይገኝበታል።
ቀደም ሲል የ8 ቢሊዮን ብር ኪሳራ ይስተዋልባቸው የነበሩት እነዚህ ድርጅቶች፣ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ውስጥ ብቻ 2.1 ትሪሊዮን ብር ገቢ ማስገኘት ችለዋል።
ይህም ተቋማቱ ከነበሩበት የኪሳራ አዙሪት ወጥተው ወደ ላቀ ትርፋማነት መሸጋገራቸውን የሚያረጋግጥ ነው።

የኢንቨስትመንት ከባቢው መሻሻልንም ተከትሎ 2,153 አዳዲስ የኢንቨስትመንት ፈቃዶች የተሰጡ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል 65 በመቶው በማምረቻው ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ናቸው።
ይህ የኢንቨስትመንት ፍሰት በዘጠኝ ወራት ውስጥ ለ96,000 ዜጎች የሥራ ዕድል የፈጠረ ሲሆን፣ የማምረቻው ዘርፍ የገበያ ድርሻም ከ25 ወደ 46 በመቶ ከፍ እንዲል አስችሏል።
በዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ረገድም ሀገሪቱ በ4ጂ እና 5ጂ የኔትወርክ ዝርጋታ፣ በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ተቋማት ግንባታና በመንግሥታዊ አገልግሎቶች ዲጂታላይዜሽን ረገድ ፈጣን ለውጥ እያስመዘገበች መሆኑ በሪፖርቱ ተብራርቷል።
በዓለም አቀፍ ደረጃም የብሪክስ (BRICS+) አባልነት፣ የኮፕ 32 (COP32) ጉባኤን ለማስተናገድ መመረጧና በንቁ ዲፕሎማሲ እየተከናወኑ ያሉ የባሕር በር የማግኘት ጥረቶች የኢትዮጵያን ተሰሚነት እያሳደጉት መሆኑ ተመላክቷል።
ባጠቃላይ የቀረበው ሪፖርት ኢትዮጵያ በመዋቅራዊ ለውጥና በዘርፍ ትራንስፎርሜሽን አማካኝነት የማይበገርና ተወዳዳሪ ኢኮኖሚ ለመገንባት የጀመረችው ጉዞ ተጨባጭ ውጤት እያመጣ መሆኑን ያረጋገጠ ነው።