ኢትዮጵያ ለአፍሪካውያን አርዓያ የሚሆን በቴክኖሎጂ የታገዘ ሰላማዊና የተሳካ ምርጫ አካሂዳለች

AMN ሰኔ 8/2018

ኢትዮጵያ ለአፍሪካውያን አርዓያ የሚሆን በቴክኖሎጂ የታገዘ ሰላማዊና የተሳካ ምርጫ ማካሄዷን በኢትዮጵያ የህንድ አምባሳደር አኒል ኩመር ራይ ገለጹ፡፡

ኢትዮጵያ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም እንደ አፍሪካ ኅብረትና ኢጋድ ያሉ አህጉራዊና ቀጣናዊ ተቋማት የምርጫ ታዛቢዎችን በማሰማራት ገለልተኛና ዲሞክራሲያዊነቱን የመሰከሩለት ጠቅላላ ምርጫ ማድረጓ ይታወሳል፡፡

በምርጫው የሀገር ውስጥ ታዛቢዎችም የተሳተፉ ሲሆን 55 የሲቪል ማህበራትን ያቀፈው የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ አሳታፊ፣ነጻና ዲሞክራሲያዊ መሆኑን መታዘቡን ገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ የጸጥታ፣ የፍትሕና የዲሞክራሲ ተቋማት ምርጫውን በገለልተኝነትና በተቋማዊ ብቃት እንዲካሄድ ማስቻላቸውን መታዘቡን አረጓግጧል፡፡

በኢትዮጵያ የህንድ አምባሳደር አኒል ኩመር ራይ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግስት የተሳካ ጠቅላላ ምርጫ ማካሄዳቸውን ገልጸዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከምርጫው በፊት አሳታፊ ምርጫ እንደሚካሄድ በገቡት ቃል መሰረት መንግሥት ለምርጫው ዲሞክራሲያዊነት ከቅድመ ምርጫ ጀምሮ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩንም አድንቀዋል።

ምርጫው በርካታ ኢትዮጵያውያን ድምጻቸውን የሰጡበት፥ የሴቶችና የወጣቶች የነቃ ተሳትፎ የታየበት መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

እንደ አፍሪካ ኅብረትና ኢጋድ ያሉ አህጉራዊና ቀጣናዊ ተቋማት የምርጫ ታዛቢዎችን በማሰማራት ምርጫው ሰላማዊና ፍትሐዊ መሆኑን ማረጋገጣቸውም የምርጫውን ዴሞክራሲያዊነት የሚያሳይ መሆኑን በአድናቆት ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ ከእጩዎችና መራጮች ምዝገባ ጀምሮ በቴክኖሎጂ የታገዘ፣ ለአፍሪካውያን አርዓያ የሚሆን ነፃ፣ ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ማካሄድ ችላለች ነው ያሉት።

የአፍሪካ ጉዳይ በአፍሪካውያን መፈታት አለበት ያሉት አምባሳደሩ፤ በኢትዮጵያ ጠቅላላ ምርጫ የአፍሪካ ኅብረት እና ኢጋድ ታዛቢዎች መሰማራታቸው የዚህ ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የሁለቱ ተቋማት የምርጫ ታዛቢዎች ያደረጉት ምልከታና አስተያየት ሁላችንም የምንቀበለው ነው ማለታቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review