AMN – ሰኔ 8/2018 ዓ.ም

በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ተሸናፊነትን የመቀበል ባህልን ለመለወጥና ለሀገር ደህንነት ቅድሚያ ለመስጠት የተፎካካሪ ፓርቲዎችና የደጋፊዎቻቸው ንቃተ-ህሊና ሊታደስ እንደሚገባ የህብር ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር አቶ አበራ በቀለ ከአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ የሰንኮፍ ፕሮግራም ጋር በነበራቸው ቆይታ ገለጹ።
አቶ አበራ በቀለ በሰንኮፍ ፕሮግራም ላይ ቀርበው በሰጡት ማብራሪያ፣ ምርጫን ማሸነፍ ማለት የመንግስት ሥልጣን ወይም ወንበር መያዝ ብቻ ሳይሆን የሀሳብ አሸናፊነትና የሀሳብ ልዕልና ጭምር መሆኑን ገልጸዋል።
በምርጫ ታሪክ ውስጥ ተቃዋሚ የሚለውን የኋላ ቀር ፅንሰ-ሀሳብ በመተው ተፎካካሪ ወደሚል የሰለጠነ ፖለቲካ መሸጋገር መቻሉን የገለጹት ምክትል ሊቀመንበሩ፣ ህዝብ ድምፅ ባይሰጥ እንኳ ያቀረቡት አማራጭ ሀሳብ የሚገዛበት መድረክ መኖሩ ራሱ ትልቅ ስኬት መሆኑን አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ካለችበት ጂኦ-ፖለቲካዊ አጣብቂኝና የውጭ ጠላቶች ጥቃት አንጻር፣ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ከምርጫ ማሸነፍ በላይ ለሀገረ-መንግስቱ ቀጣይነትና ለጠንካራ ስርዓተ-መንግስት ምስረታ ቅድሚያ ሊሰጡ እንደሚገባም አሳስበዋል።
አቶ አበራ በቀለ በማብራሪያቸው፣ ቀደም ሲል በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የነበረው ገዢ እና ተቃዋሚ የመካካድ ስሜት በሂደትና በጋራ የምክር ቤት እንቅስቃሴዎች ተለውጦ ወደ ተፎካካሪነት መምጣት ችሏል።
ይህ ለውጥ ፓርቲዎች የሰለጠነ ርዕዮተ-ዓለምና ማኒፌስቶ ይዘው እንዲቀርቡና ትግላቸውን በጦርነት ሳይሆን በሀሳብ፣ በስክሪፕቶና በጠረጴዛ ዙሪያ ብቻ እንዲያደርጉ በር ከፍቷል ብለዋል።
የአሸናፊነት ስነ-ልቦና ትርጉም ሊታደስ እንደሚገባ የገለጹት አቶ አበራ፣ የፖሊሲ አማራጮችን ለህዝብ ማቅረብና የሚያምኑ ሰዎችን ቁጥር እየጨመሩ መሄድ ራሱ ትልቅ የአሸናፊነት ምሳሌ መሆኑን ጠቅሰዋል።
አክለውም ህዝብ ድምፅ አልሰጠም ማለት መሸነፍ አለመሆኑን ጠቁመው የአሸናፊነት ስነ-ልቦና የመንግስት መቀመጫን መያዝ ብቻ ሳይሆን የሀሳብ ልዕልና ጭምር መሆኑን ተናግረዋል።
በምርጫው ወቅት ፓርቲዎችን ለማስፈራራትና ወደ ምርጫ እንዳይገቡ ለማድረግ የሞከሩ ጽንፈኛ ኃይሎች መኖራቸውን ያስታወሱት ምክትል ሊቀመንበሩ፣ እነዚህ አካላት የውስጥ ጥያቄዎችን ሽፋን በማድረግ የውጭ ታሪካዊ ጠላቶችን አጀንዳ በእጅ አዙር የሚያስፈጽሙ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
በመሆኑም በሃያ አንደኛው ክፍለ-ዘመን ጉዳይን በጉልበትና በጫካ ለማስፈጸም መሞከር ሊቆም እንደሚገባና ሁሉም ፓርቲ ሀገረ-መንግስት የሚባለውን ትልቅ ፅንሰ-ሀሳብና ስነ-ልቦና ሊታጠቅ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ሀገር እንድትቀጥል፣ የውስጥ ሰላምና የውጭ ጥቅሟ እንዲከበር ጠንካራ ስርዓተ-መንግስት መመስረት ስላለበት ምርጫ ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል።
በመጨረሻም፣ ህብረ ኢትዮጵያም ሆነ ሌሎች ፓርቲዎች መቶ ፐርሰንት አሸንፋለሁ በሚል ስሌት ብቻ ሳይሆን ሀገር እንድትቀጥልና ሀሳባቸውን በአግባቡ ለመሸጥ ወደ ምርጫ መግባታቸውን የገለጹት አቶ አበራ፣ በየትኛውም አውድ የሚመጣው አሸናፊ አካል ለህዝብ የሚጠቅመውን ሀሳብ መግዛት እንዳለበትና ሁልጊዜም ኢትዮጵያዊነት ላይ የተመሰረቱ ፅንሰ-ሀሳቦች ሊራመዱ እንደሚገባ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
በወርቅነህ አቢዮ