በአዲስ አበባ ከታቀደው በላይ ዜጎች የ5 ሚሊዮን ኮደርስ ስልጠናን ለመውሰድ ተመዝግበዋል

AMN- ሰኔ 9/2018 ዓ.ም

በአዲስ አበባ በእቅድ ከተያዘው በላይ ዜጎች የአምስት ሚሊዮን ኮደርስ ስልጠናን ለመውሰድ መመዝገባቸውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ አስታወቀ።

በከተማዋ ከ809 ሺህ በላይ ዜጎች የአምስት ሚሊየን ኮደርስ ስልጠናን እንዲወስዱ ለማድረግ ታቅዶ፣ ከ996 ሺህ በላይ ዜጎች ስልጠናውን ለመውሰድ መመዝገባቸውን ቢሮው ገልጿል።

እስከ አሁን ባለው ሂደት ስልጠናውን ለመውሰድ ከተመዘገቡት ዜጎች መካከል 742 ሺህ የሚሆኑት ስልጠናውን በማጠናቀቅ የምስክር ወረቀት ወስደዋል።

ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የዲጂታል ምህዳር ውስጥ ንቁ ተሳታፊና ተወዳዳሪ ለመሆን በዲጂታል መሠረተ ልማትና በዲጂታል ክህሎት እየተዘጋጀች ነው።

የዚህ ብሔራዊ ግብ አካል የሆነው የአምስት ሚሊየን ኮደርስ መርኃ-ግብር ሐምሌ 16 ቀን 2016 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በይፋ መጀመሩ ይታወሳል።

ይህም በሦስት ዓመታት ውስጥ በሀገር አቀፍ ደረጃ 5 ሚሊየን ወጣቶች በኦንላይን የኮዲንግ ስልጠና እንዲወስዱ ዓላማ ያነገበ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቅርቡ ባስተላለፉት መልዕክት በመርኃ-ግብሩ ‎በሦስት ዓመታት ውስጥ ለማሳካት የታቀደውን ግብ ከሁለት ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ማሳካት ተችሏል ብለዋል።

በመርኃ-ግብሩ ከ5 ሚሊየን በላይ ሰልጣኞች ተመዝግበው ከ3 ሚሊየን በላይ የሚሆኑት ስልጠናውን ማጠናቀቃቸውንና ይህ ስኬት የሕዝቡ ቁርጠኝነት እና ወሰን የሌለው አቅም ማረጋገጫ መሆኑን ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ እና የስማርት ሲቲ ዘርፍ ኃላፊ ቱሉ ጥላሁን (ዶ/ር) እንዳሉት፤ የኮደርስ ስልጠናዎች የዲጂታል ክህሎትን ከማሳደጋቸው በተጨማሪ የፈጠራ ሃሳብን የሚያጎለብቱና ቴክኖሎጂ ለማልማት የሚችሉበት እድል የሚፈጥር ነው።

በአዲስ አበባ ከ800 ሺህ በላይ የሰው ኃይልን ለማሰልጠን መታቀዱን ጠቅሰው፣ እስከ አሁን ባለው መረጃ ከ90 በመቶ የሚልቁ ዜጎች ስልጠናቸውን ማጠናቀቃቸውን ገልፀዋል።

በከተማዋ የአምስት ሚሊየን ኮደርስ እቅድን ለማሳካት ቢሮው ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሠራ መሆኑንም አንስተዋል።

ቢሮው የዜጎችን የዲጂታል ክህሎት የሚያጠናክሩ ሌሎች ዘመናዊ ስርዓቶችን ወደተግባር በማስገባት ስልጠና ለመስጠት ማቀዱንም ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እስከ ነሐሴ 2018 ዓ.ም ድረስ የኮደርስ ሰልጣኞችን ቁጥር 7 ሚሊየን ለማድረስ መታቀዱንና ይህንን ብሔራዊ ተልዕኮ ለማሳካትም ዜጎች በንቃት እንዲሳተፉ ጥሪ ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review