የአንጋፋው አትሌት ሻለቃ ባሻ ዋሚ ቢራቱ የ65 ዓመታት አሻራ

You are currently viewing የአንጋፋው አትሌት ሻለቃ ባሻ ዋሚ ቢራቱ የ65 ዓመታት አሻራ

​AMN – ሰኔ 18/2018 ዓ.ም

​አንጋፋው አትሌት ሻለቃ ባሻ ዋሚ ቢራቱ ከ65 ዓመታት በፊት በጃፓን ኦሳካ ከተማ በባዶ እግራቸው በመሮጥ ያስመዘገቡትን ታሪካዊ ድል ለመዘከር የተዘጋጀው መርሃ ግብር በሀይሌ ግራንድ ሆቴል ተካሂዷል።

​በዚህ መርሃ ግብር ላይ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የአማካሪ ዴኤታ አቶ ፀጋዬ ማሞ ፣ በኢትዮጵያ የጃፓን ምክትል አምባሳደር ኔትሱ ሹንታሮ እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

መርሃ ግብሩ ላለፉት 65 ዓመታት በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ውስጥ ላበረከቱት አስተዋጽኦ እና ለሰሩት ስራ እውቅና ለመስጠት እንደተዘጋጀ የባሻ ዋሚ ቢራቱ ልጅ የሆኑት ጃጋማ ዋሚ ቢራቱ ተናግረዋል።

​በጃፓን ኦሳካ በባዶ እግር በመሮጥ የሻምበል አበበ ቢቂላን ፈለግ በመከተል የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ በአለም አቀፍ ደረጃ ከፍ እንዲል የተደረገበትን ታሪክ ማስታወስ የመርሃግብሩ ሌላኛው ዓላማ እንደሆነ ጃግማ ዋሚ ቢራቱ ገልፀዋል።

​የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የአማካሪ ዴኤታ አቶ ፀጋዬ ማሞ በበኩላቸው፥ አትሌት ዋሚ ቢራቱ በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ታሪክ ውስጥ የማይረሳ ስራ የሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል። ይህ ዝግጅትም መንግስት እና ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጀግና አትሌቶችን የማስታወስና የማክበር ኃላፊነት እንዳለባቸው ያሳየ ነው ብለዋል።

​በሌላ በኩል በኢትዮጵያ የጃፓን ምክትል አምባሳደር ኔትሱ ሹንታሮ፥ የአትሌት ዋሚ ቢራቱን የ65ኛ ዓመት የባዶ እግር አሻራ መታሰቢያ በዓል ላይ በመገኘታቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው፤ አትሌቱ ሙሉ ህይወታቸውን ለአትሌቲክስ መስጠታቸው እጅግ የሚያደንቅ ነው ብለዋል።

​በሩጫው ሜዳ ንጉስ የነበሩት ሻለቃ ባሻ ዋሚ ቢራቱ በ1909 ዓ.ም ነበር የተወለዱት።

​በተገኝ በፈቃዱ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review