AMN- ሐምሌ 6/2018 ዓ.ም

ከንቲባ አዳነች አቤቤ ፣ በአዲስ አበባ ምክር ቤት ሁለተኛ ቀን ውሎ የቀረበውን የኦዲት አፈጻጸም ሪፖርት አስመልክተው በሰጡት አሰስተያየት 107 ተቋማት በአንድ አመት ኦዲት መደረጋቸው ትልቅ መሻሻል መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ኦዲት የተደረጉ ተቋማት ያለባቸው ግኝት ላይ ክትትል መደረጉም ተቋማቱ ራሳቸውን እንዲያሻሽሉ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ገልጸዋል፡፡

ኦዲት ከተደረጉት መካከል 26 ተቋማት በኦዲት ሪፖርት ነቀፌታ ያልተገኘባቸው እና 49 ተቋማትም ጉልህ ነቀፌታ የሌለባቸው መሆኑ ትልቅ ስኬት መሆኑን ከንቲባዋ ገልጸዋል፡፡
31 ተቋማት ሰነድ ሳያቀርቡ ፣ ለኦዲት ክብር ሳይሰጡ ፣ ውስጥ ባለባቸው ችግር ምክንያት ክፍተት የታየባቸው መታረም እንዳለባቸውም ከንቲባ አዳነች አቤቤ አሳስበዋል፡፡

ግኝቶቹ ጠንከር ያለ ክትትል ቢደረግ ሊታረሙ የሚችሉ መሆናቸውን በማንሳት በቀጣይ ክትትልና ድጋፍ በማድረግ ተቋማትን የማብቃትና የማስተካከል ስራዎች መከናወን እንዳለባቸውም ገልጸዋል፡፡
ተጠያቂነት ሊሰፍነባቸው የሚገባ ግኝቶችም መኖራቸውን የጠቀሱት ከንቲባዋ በእነዚህ ላይ ተጠያቂነት የማስፈን ስራዎች እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡
በጥቅሉ የኦዲት አፈጻጸም ሪፖርቱ የከተማዋ የሐብት አጠቃቀምና የገቢና ወጪ አስተዳደር ጤናማ መሆኑን የሚያመላክት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ታደሠ ሽፈራው