AMN ሐምሌ 06/2018 ዓ.ም

በፌዴራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን የከፍተኛ ጥበቃ ማረሚያ ማዕከል እና ሴቶች ማረፊያና ማረሚያ ማዕከል በመደበኛ የትምህርት መርሃ ግብር ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የነበሩ 40 የህግ ታራሚ ተማሪዎች የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና በመውሰድ ላይ ይገኛሉ።

በኮሚሽኑ የትምህርትና ስልጠና መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ አዝመራ አብደታ እንደገለፁት ፈተናውን እየወሰዱ ከሚገኙ 40 የህግ ታራሚ ተማሪዎች መካከል 10 የሚሆኑት ሴቶች መሆናቸውን አስረድተዋል።

የአዲስ አበባ ማረሚያ ብሩህ ነገ ቅድመ አንደኛና አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አቶ ሳምሶን ወንድሜነህ በበኩላቸው ትምህርት ቤቱ ደረጃውን ጠብቆ በተሟላ የመማር ማስተማር ሂደት ላይ መሆኑን ገልፀው፤ የህግ ታራሚ ተማሪዎች በህግ ጥላ ስር ሆነው ትምህርታቸውን በአግባቡ ሲከታተሉ መቆየታቸውን ተናግረዋል፡፡

ከዚህ በፊት በኮሚሽኑ የማረሚያ ማዕከላት ውስጥ በእርምት ሂደት ላይ ሆነው መደበኛ ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የነበሩና 74 የሚሆኑ የ6ኛ እና የ8ኛ ክፍል የህግ ታራሚ ተማሪዎች ክልላዊ የመልቂያ ፈተና በመውሰድ ሙሉ በሙሉ የማለፊያ ውጤት ማምጣታቸውን ጨምረዉ ገልጸዋል።
በማረሚያ ቤት ውስጥ የሚገኘው የአዲስ አበባ ማረሚያ ብሩህ ነገ ቅድመ አንደኛና አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መደበኛ ትምህርታቸውን የሚከታተሉ የ6ኛ ክፍል ፣ የ8ኛ ክፍል እና የ12ኛ ክፍል የህግ ታራሚ ተማሪዎች ሀገራዊና ክልላዊ የመውጫ ፈተናዎችን የሚሰጥበት የትምህርት ተቋም መሆኑ ልዩ እንደሚያደርገው ማመላከታቸዉን ከፌዴራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን ይፋዊ ትስስር ገጽያገኘነዉ መረጃ ያሳያል።