ከሽኩቻ ወደ ጋራ ራዕይ – ኢትዮጵያ በምክክር

AMN- ሐምሌ 7/2018 ዓ.ም

የሰው ልጅ ታሪክ እንደሚያስተምረን፣ ማናቸውም ዘላቂና አስተማማኝ መፍትሄዎች የሚመነጩት ከጦር አውድማ ሳይሆን ከምክክር አውዶች ነው።

ልዩነቶች የተፈጥሮ ነፀብራቅ ናቸው ፤ ይሁን እንጂ እነዚህን ልዩነቶች የምናስተናግድበት መንገድ የሀገርን መጻኢ እድል ይወሰናል። ዛሬ ላይ ቆመን ወደኋላ ስንመለከትም ሆነ ወደፊት ስናማትር፣ ለሀገራዊ አንድነትና ለጋራ እድገት ፍቱን መድኃኒት ሆኖ የምናገኘው አንድ ነገር ብቻ ነው ፤ እሱም ብሔራዊ ምክክርና እውነተኛ ውይይት ነው።

ምክክር ከተለያዩ ወገኖች የሚነሱ አማራጮችን አቀናጅቶ ወደ መፍትሄና የጋራ ውሳኔ ለመድረስ የሚደረግ ጥልቅ ሂደት ነው። ልዩነቶችን በምክክር መፍታት የጋራ ባለቤትነትን ለመፍጠር ፣ ጥርጣሬንና አለመተማመንን ለማስወገድ እና አካታችነትን ለማረጋገጥ የሚያስችል ጠቀሜታ አለው፡፡

ሁሉም ወገን በውሳኔ አሰጣጥ ሂደት ላይ ሲሳተፍ ፣ የተደረሰበትን ስምምነት የመጠበቅና የማክበር ኃላፊነት ይሰማዋል። ፊት ለፊት መነጋገር በሩቅ ሳሉ የሚፈጠሩ የጥርጣሬ ደመናዎችን ይበትናል። ሁሉንም ማሕበረሰብ ያካተተ መሆኑ የአናሳ ወይም የደካማ ድምፆች ሳይቀሩ እንዲደመጡ ዕድል ይሰጣል።

አለመግባባቶችን በሃይል ለመፍታት መሞከር ጊዜያዊ የበላይነትን ቢያስገኝ እንጂ ዘላቂ ሰላምን ሊያመጣ አይችልም። እውነተኛ ሰላም የሚወለደው የሌላውን ሃሳብ ለመስማት ፈቃደኛ ከሆነ ማሕበረሰብ ነው፡፡

በአንድ ሐገር ውስጥ ፖለቲካዊ ልዩነቶች መኖራቸው ተፈጥሯዊና የአንድን ማህበረሰብ ህያውነት የሚያሳዩ ናቸው። ታዲያ እነዚህ ልዩነቶች ወደ ጥላቻና ግጭት እንዳያመሩ የንግግር ባህልን ማሳደግ ግድ ይላል።

በጠረጴዛ ዙሪያ የሚቀመጡ ኃይሎች የራሳቸውን ፍላጎት ብቻ ይዘው ሳይሆን ፣ የሀገርንና የህዝብን የጋራ ደህንነት አስቀድመው መሆን አለበት።

የጋራ ሀገረ-መንግስት ማለት ሁሉም ዜጋ እኩል የሚታይበት ፣ ማንነቱና መብቱ የሚከበርበት እንዲሁም “ይህች ሀገር የእኔም ናት” ብሎ በኩራት የሚኖርባት ማዕቀፍ ማለት ነው። እንዲህ ዓይነቱ ጠንካራ ሀገረ-መንግስት የሚገነባው ደግሞ መሰረቱ በምክክር የጸና ሲሆን ነው።

በምክክር የሚመሰረት ሀገረ መንግስት ፣ ታሪካዊ ጠባሳዎችን በጋራ ፈውሶ፣ ወደ ፊት የሚያራምድ የጋራ ታሪክና ራዕይ ይቀርጻል ፣ ለሁሉም ዜጋ እኩል የሚያገለግሉ ገለልተኛና ጠንካራ ተቋማትን ይገነባል ፣ የሀገሪቱ የበላይ ህግ በሁሉም ዜጎችና ስብስቦች ዘንድ ቅቡልነት እንዲኖረው ያደርጋል።

ኢትዮጵያውያንም ይህ እውን ሊያደርጉ ተዘጋጅተዋል። ከመላ ኢትዮጵያ የተወጣጡ 4 ሺህ የማሕበረሰብ ተወካዮች ሐምሌ 8 ምክክራቸውን ለመጀመር አዲስ አበባ ከትመዋል፡፡ ምክክሩ ለዘመናት የዘለቀችው ኢትዮጵያን ፣ በማይናወጥ መሠረት ላይ እንደሚያጸናት ተስፋ ተደርጓል፡፡

ታደሠ ሽፈራው

See less

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review