AMN – ሐምሌ 8/2018 ዓ.ም
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ መጀመርን አስመልክተው በማሕበራዊ ትስስር ገጻቸው መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው ፣ ልሂቃን በሚፈጥሩት ግጭት ሕዝባችን ቢታመስም ባህላችን ግን ለምክክር ያደላ ነበር ብለዋል።
ቤታችን፣ ሞሰባችን፣ አቀማመጣችን፣ ማብሰያችን፣ ወዘተ. ክብ ናቸው ሲሉ የጠቀሱት አቶ ተመስገን ፣ ይሄውም ነገርን ሰብሰብ ብሎ በመመካከር ለመከወን እንዲያመች የተሠራ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

ክብ መነሻና መድረሻ የለውም። ሩቅና ቅርብ የለውም። ወጪና ገቢ የለውም። ሁሉንም በእኩልነት ያሳትፋል ሲሉም አብራርተዋል።
ይሄን የተረሳ ባህላችንን ወደ ሀገራዊ ምክክር አምጥተነዋል በማለት የጠቀሱት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፣ ኢትዮጵያውያን ከአራቱም ማዕዘን መጥተው በጋራ ይመክራሉ ብለዋል።
እሺ በጄ ያለ ሁሉ ዕድል ተሰጥቶታል ፤ እነሆ ኢትዮጵያ በኢትዮጵያውያን ለነገ እንድትሆን ሆና ልትገነባ ተሰባስባለች ብለዋል።
የሀገር ጸሎት ልብና ጆሮ ከእናንተ ጋራ ነው ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።