AMN – ሐምሌ 8/2018 ዓ.ም
የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ-መንግሥታት (ኢጋድ) ዋና ጸሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር)፣ በኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር መድረክ ላይ ባደረጉት ንግግር ምክክሩ በሀገሪቱ ታሪክ ውስጥ አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት መሆኑን ገልጸዋል።
ዋና ጸሐፊው በንግግራቸው፤ ለሀገራዊ ችግሮች ዘላቂ መፍትሔ ለማግኘት ወደ ውጭ ከመመልከት ይልቅ፣ ወደ ውስጥ ወደ ሀገር በቀል እሴቶች መዞር እንደሚገባ ተናግረዋል።
ብዝሃነት ባለው ማኅበረሰብ ውስጥ የተለያየ አመለካከት መኖሩ ተፈጥሯዊ መሆኑን የጠቀሱት ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር)፤ ዋናው ቁምነገር ልዩነቶችን የሚፈቱበት መንገድ ላይ መሆኑን አስገንዝበዋል።

በመሆኑም ልዩነቶችን በኃይልና በጠመንጃ ለመፍታት መሞከር መሠረታዊ ስህተት መሆኑን በመረዳት፣ በምትኩ በንግግርና በውይይት ችግሮችን የመፍታት አዲስ የፖለቲካ ባህል መገንባት እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።
በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ እናቶች፣ አባቶችና ሕፃናት በተለያዩ ችግሮች ውስጥ ሆነው የዚህን መድረክ ውጤት በታላቅ ጉጉት እየተጠባበቁ መሆኑን ዋና ጸሐፊው ተናግረዋል።
በመሆኑም በመድረኩ ላይ የተሳተፉ አካላት ሁሉ ይህንን ከባድ ሀገራዊና ታሪካዊ ኃላፊነት በከፍተኛ ቁርጠኝነት ሊወጡ እንደሚገባ አሳስበዋል።

አዲሱ የኢትዮጵያ ታሪክ በውይይትና በንግግር ተጽፎ ለሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም እንደሚያመጣ ሙሉ እምነት እንዳላቸው የገለጹት ዋና ጸሐፊው ፤ ኢጋድ በዚህ ታሪካዊ የሰላም ጉዞ ውስጥ ከኢትዮጵያ ጎን በጽናት እንደሚቆም አረጋግጠዋል።
የዚህ ምክክር ስኬታማነት ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን መላውን የአፍሪካ ቀንድ ቀጠና ወደ ብሩህ ተስፋና ብልጽግና የሚመራ ታላቅ እርምጃ መሆኑንም ገልጸዋል።
በበረከት ጌታቸው