በትግራይ ክልል አፈሳ፣ አፈና እና ጭቆና – እስከመቼ?

AMN – ሐምሌ 16/2018 ዓ.ም

የሰሜኑን ጦርነት ዳግም ለማስነሳት እንቅልፍ ያጡ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች፣ ዛሬም የጥፋት ሴራቸውን እየጠነሰሱ ይገኛሉ።

ከጦርነትና ከግጭት ትርፍ የሚሹት እነዚህ ኃይሎች፣ የሰላምን አየር ማጣጣም የጀመረውን የትግራይ ሕዝብ ዳግም ወደ እልቂት ለማስገባት አልመዋል።

ከዚህ ቀደም ለአገር ሰላም ሲባል የተደረሰው የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት፣ በርካታ አዎንታዊ ውጤቶችን ያስገኘ የሰላም ማዕቀፍ ነው።

ስምምነቱን ተከትሎ የፌደራል መንግሥት በችግር ውስጥ ለነበሩ የታጠቁ ኃይሎች ሰፊ ድጋፍ በማድረግ ለሰላም ያለውን ቁርጠኝነት በተግባር አሳይቷል።

በተጨማሪም በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲቋቋም በማድረግ ተቋርጠው የነበሩ መሠረታዊ አገልግሎቶች እንዲመለሱ ተደርጓል፤ በዚህም የትግራይ ሕዝብ የሰላም አየር መተንፈስ ችሏል።

ሆኖም ሕገ-ወጡ የሕወሓት ቡድን ስምምነቱን በመጣስ ዳግም በክልሉ ጦርነት ለማስነሳት እየሰራ ይገኛል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው በሰጡት ማብራሪያ፤ የፌደራል መንግሥት በሆደ-ሰፊነት ለሰላም ብዙ ዋጋ መክፈሉን ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም፣ በትግራይ ባሉ ኃይሎች በየቀኑ አዳዲስ ግጭቶችን ሊቀሰቅሱ የሚችሉ ትንኮሳዎች እየተፈጸሙ መሆናቸውን እና በርካታ የትግራይ ክልል ልጆች በጉልበት ታፍሰው ወደ ሱዳን ጦርነት መሸጣቸውን ጠቁመዋል።

ቡድኑ የፕሪቶሪያውን ስምምነት በመጣስ እና ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር በመተባበር እየፈጸመ ባለው እኩይ ተግባር፣ የትግራይ ክልል ወጣቶች በማያውቁት ጉዳይ በሱዳን ጦርነት ውስጥ ሕይወታቸውን እያጡ ይገኛሉ።

የትግራይ እናቶችም ልጆቻቸው በድጋሚ ለጦርነት ማገዶ ሲሆኑ ማየት ትልቅ ሕመም ሆኖባቸዋል።

ይህንኑ ተከትሎ በአዲስ አበባ የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች ቡድኑ በትግራይ ወጣቶች ላይ እያደረሰ ያለውን አፈሳ፣ አፈና እና ጭቆና በመቃወም በቅርቡ ሰላማዊ ሰልፍ አካሂደዋል።

የችግሩ ፈጣሪ ሳይሆን የችግሩ ገፈት ቀማሽ የሆነው የትግራይ ሕዝብ፣ በአዲስ አበባና በሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚታዩ የልማት ሥራዎች በትግራይም ተደራሽ ሆነው ማየት የመንግሥትና የሕዝብ የጋራ ፍላጎት ነው።

ይህ እውን ይሆን ዘንድም፣ በተለይ የትግራይ ክልል ወጣቶች ለፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ተፈጻሚነትና ለዘላቂ ሰላም መረጋገጥ ከፌዴራል መንግሥት ጎን ሊቆሙ ይገባል፡፡

የበለጸገች፣ ሰላሟ የተረጋገጠ እና የታፈረች ኢትዮጵያን ለትውልድ ለማሻገር ኢትዮጵያውያን አንድነታቸውን ማጠናከር እና ለብሔራዊ ጥቅም ቅድሚያ መስጠት ይጠበቅባቸዋል።

በትዝታ መንግስቱ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review