AMN – ሐምሌ 17/2018

የትምህርት ቤቶችን መዘጋት ተከትሎ በርካታ ህጻናትና ታዳጊዎች አብዛኛውን የክረምት የእረፍት ጊዜያቸውን በስልክ፣ በታብሌት፣ በላፕቶፕ እና በቴሌቪዥን መስኮት ፊት ማሳለፋቸው በስፋት እየተስተዋለ ይገኛል።
ይህ ሁኔታ በብዙ ወላጆች ዘንድ ልጆች ጊዜያቸውን የሚያሳልፉበት ቀላል አማራጭ ተደርጎ ቢወሰድም፤ በልጆች አእምሯዊ እድገት፣ ንግግር፣ ስሜት እና ማህበራዊ መስተጋብር ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደረ መሆኑን ባለሙያዎች ይገልፃሉ።

በፍጥነት የሚቀያየሩ የስክሪን ምስሎች የልጆችን የማተኮር አቅም የሚቀንሱ በመሆናቸው እንደ ትምህርት እና ንባብ ባሉ ትኩረት በሚሹ እንቅስቃሴዎች ላይ እንዳያተኩሩ ከማድረጋቸውም በላይ የችግር መፍታት እና የፈጠራ አቅማቸውን ያዳክማሉ።
ከልክ ያለፈ የስክሪን እይታ በተለይ በህጻናት ላይ ሃሳብን የመግለጽ፣ የመግባባት እና የሰዎችን ስሜት የመረዳት አቅምን ይቀንሳል።
ከመኝታ በፊት የሚደረግ የኤሌክትሮኒክስ መሣሪያዎች አጠቃቀም የእንቅልፍ ስርዓትን በማስተጓጎል ለአእምሮ መዳከም ቀጥተኛ ምክንያት ይሆናል፡፡

ኤሌክትሮኒክስን አብዝቶ መጠቀም ደግሞ በአንጎል ውስጥ የደስታ ሆርሞን መዛባትን በመፈጥር መሣሪያዎቹ በሚወሰዱበት ጊዜ ልጆች ከፍተኛ ቁጣ፣ ብስጭት እና የባህሪ መለዋወጥ እንዲያሳዩ ያደርጋቸዋል።
ከእኩዮቻቸው ይልቅ ከስክሪን ጋር ብቻ ጊዜ የሚያሳልፉ ልጆች የመቻቻል ባህሪያቸው ከመቀነሱም በላይ ለአካላዊ ብቃት ማነስ እና ከመጠን ላለፈ ውፍረት ይዳረጋሉ።

ይህንን ስጋት ለመቀነስ እና የልጆችን የክረምት ጊዜ ፍሬያማ ለማድረግ ወላጆች ልጆች ከስክሪን ጋር የሚያሳልፉትን ጊዜ እንደ ዕድሜያቸው መጠን መገደብ እና ከመኝታ ሰዓት በፊት ማንኛውንም የኤሌክትሮኒክስ መሣሪያ መጠቀምን በፍጹም መከልከል እንዳለባቸው ባለሙያዎች ይጠቁማሉ።
ይልቁንም በአእምሮ የሚሰሩና የሚገጣጠሙ መጫወቻዎችን፣ የፈጠራ እና የስዕል ስራዎችን እንዲሁም የንባብ ልምድን ማዳበር አስፈላጊ ነው።
በተመሳሳይ መልኩ ልጆች ከእኩዮቻቸው ጋር የሚጫወቱባቸውን የሜዳ ላይ ጨዋታዎችና የስፖርት እንቅስቃሴዎች ማመቻቸት፣ በቤት ውስጥ እንደ ዕድሜያቸው መጠን ቀላል ኃላፊነቶችን መስጠት እና የቤተሰብ ጊዜያትን ያለ ስልክ ማሳለፍ ይገባል።
ከሁሉም በላይ ግን ወላጆች በቤት ውስጥ የራሳቸውን የኤሌክትሮኒክስ መሣሪያዎች አጠቃቀም በመቀነስ ለልጆቻቸው አርአያ በመሆን የልጆቻቸውን የክረምት ጊዜ ፍሬያማ ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡
በበረከት ጌታቸዉ