AMN- ሐምሌ 19/2018 ዓ.ም
በየዓመቱ ሐምሌ 19 ቀን የሚከበረው የቅዱስ ገብርኤል ዓመታዊ የንግሥ በዓል፣ በሐዋሳ ደብረ ምህረት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም እና በቁልቢ ደብረ ኃይል ቅዱስ ገብርኤል ገዳም በተለያዩ ሃይማኖታዊ ሥነ-ስርዓቶች ተከብሯል።
በዓሉ የሃይማኖት አባቶች፣ ምዕመናን እንዲሁም የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገራት እንግዶች በተገኙበት በመንፈሳዊ ሥነ-ስርዓት ተከናውኗል።
በቁልቢ ቅዱስ ገብርኤል ገዳም እየተካሄደ ባለው የንግሥ በዓል ሥርዓት ላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ጠቅላይ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ፣ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ እና ሌሎች ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ተገኝተዋል።

በሐዋሳ ከተማ እየተከበረ በሚገኘው የንግሥ በዓል ላይ የሲዳማ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ ተገኝተው በዓሉን ከምዕመናን ጋር በጋራ አክብረዋል።
የቅዱስ ገብርኤል ዓመታዊ የንግሥ በዓል በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎችም በተለያዩ መንፈሳዊ ሥርዓቶች ተከብሯል፡፡