ፕሮጀክቱ ከዘመናዊ ተርሚናል በላይ ትርጉም አለው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

AMN- ሐምሌ 30/2018 ዓ.ም

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የባሕር ዳር ደጃዝማች በላይ ዘለቀ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አዲሱን ተርሚናል መረቁ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፤ ይህ ፕሮጀክት ከዘመናዊ ተርሚናል በላይ ትርጉም አለው ብለዋል።

አዲሱ ተርሚናል ለኢትዮጵያ ቁልፍ የበረራ በሮች አንዱ ለሆነው ለዚህ አውሮፕላን ማረፊያ ትልቅ ምዕራፍ መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡

ባሕር ዳር በቅርብ ጊዜያት ካስተናገደቻቸው ፈተናዎች ማግስት፤ የዚህ ተርሚናል ግንባታ ተጠናቆ አገልግልት መጀመር የፅናት፣ የማገገም እና ቀጣይነት ያለው ኢንቨስትመንት ማረጋገጫ ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡

አዲሱ ተርሚናል ሰፊ የአውሮፕላን ማቆሚያዎችን፣ የላቁ መሰረተ ልማቶችን፣ የተስተካከሉ መዳረሻ መንገዶችን እና ዘመናዊ መገልገያዎችን ያካተተ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡

ይህም የአውሮፕላን ማረፊያውን የመቀበል ዐቅም በማሳደግ የአካባቢውን እያደገ የመጣ ፍላጎት የሚያሟላ ነው ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡

ለመንገደኞችም ምቹና ቀልጣፋ አገልግሎት ይሰጣል ነው ያሉት፡፡

ይህ አዲስ ተርሚናል ከተማዋን እያደሰ ካለው የከተማ ትራንስፎርሜሽን ጋር ተዳምሮ፤ ባሕር ዳርን ለዓለም አቀፍ እና ለሀገር ውስጥ በረራዎች ሌላኛዋ ቁልፍ መዳረሻና ማዕከል ያደርጋታል ብለዋል በመልዕክታቸው፡፡

ባሕር ዳርን የመሰለች ንቁ ከተማ የምታስገኘውን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለማረጋገጥ የአካባቢው ማህበረሰብ ሰላሙን መጠበቁን እንደሚቀጥል ተስፋ አደርጋለሁ ሲሉም ገልጸዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review