AMN- ግንቦት 02/2018 ዓ.ም
አዲስ አበባ ራሷን እየቀየረች ያለችው በተለያዩ መሰረተ ልማቶች ብቻ ሳይሆን፣ በነገው የአገር ተስፋ በሕፃናት ልብ ውስጥም ጭምር ነው። ይህቺ የዲፕሎማሲ መዲና የዓለም አቀፉን የቀዳማዊ ልጅነት ልማት ጉባኤን ለማስተናገድ የተመረጠችው በታሪኳ ብቻ ሳይሆን፣ ዛሬ ለሕፃናት እያደረገችው ባለው ተግባራዊ ለውጥ ጭምር ነው።
ከተማዋ ለዚህ ታላቅ ጉባኤ ዝግጁ እንድትሆን ካስቻሏት መስፈርቶች መካከል ባለፉት ጥቂት ዓመታት የከተማ ውበትን ከሰው ተኮር ልማት ጋር በማቀናጀት የተከናወኑ የፖሊሲ ስኬቶች ለአብነት የሚጠቀሱ ናቸው።
በተለይም በከተማዋ ተግባራዊ እየሆነ ያለው የኮሪደር ልማት፣ ትምህርት ቤቶች እና የጤና ተቋማት ለሕፃናት ምቹ መሆናቸው ለዚህ ታላቅ መድረክ እንድትመረጥ ዋነኛ ምክንያቶች መሆናቸውም ተመላክቷል፡፡

በቅርቡ በተከናወነው የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት ከ48 ኪሎ ሜትር በላይ የሚሸፍኑ ሰፋፊ የእግረኛ እና የብስክሌት መንገዶች መገንባታቸው ይታወቃል፡፡
እነዚህ መሠረተ ልማቶች ሕፃናት ከቤታቸው ወደ ትምህርት ቤት እና መጫወቻ ስፍራዎች ያለምንም ስጋት እንዲንቀሳቀሱ በማስቻላቸው ለሕፃናት ምቹ ከተማ በሚል መስፈርት ከፍተኛ እውቅና እንዳስገኙላትም መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡
የከተማ አስተዳደሩ የቀዳማዊ ልጅነት ልማት ስትራቴጂን ተግባራዊ እያደረገ መገኘቱ እና ከ700 ሺ በላይ ተማሪዎችን በየቀኑ የሚመግብበት የተማሪዎች ምገባ ኤጀንሲ አንዱ ስኬታማ ተግባር ሲሆን፣ የዓለም የምግብ ፕሮግራም እና ሌሎች ድርጅቶች የአዲስ አበባን የምገባ ፕሮግራም በአፍሪካ እንደ ትልቅ ተሞክሮ ሲጠቅሱት መቆየታቸው ይታወሳል።

እንደ ወዳጅነት መናፈሻ፣ እንጦጦ ፓርክ እና አብርሆት ቤተ መጻሕፍት ያሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ለሕፃናት ልዩ ትኩረት ሰጥተው መገንባታቸው ሕፃናት በእውቀትና በጨዋታ ታንጸው እንዲያድጉ የሚያደርጉ ማዕከላት ተደርገው ይወሰዳሉ።
ሌላው ኢትዮጵያ ተግባራዊ እያደረገችው ያለው የዲጂታል መታወቂያ ስርዓት ሕፃናት ገና ሲወለዱ ጀምሮ እንዲመዘገቡ እና የጤና እንዲሁም የትምህርት አገልግሎቶችን በፍትሃዊነት እንዲያገኙ የሚያስችል መሰረት እየጣለ መሆኑም ልዩ ትኩረት ተሰጥቶታል።
ስለ ጉባኤው ዓላማና ስለ ምርጫው ሂደት የአፍሪካ የቀዳማዊ ልጅነት ልማት ኔትወርክ ባወጣው መግለጫ፤ አዲስ አበባ በዘርፉ እያሳየች ያለው መሻሻል ለአህጉሪቱ አርአያ የሚሆን መሆኑን አረጋግጧል።

አዲስ አበባ የአፍሪካ ሕብረት መቀመጫ እንደመሆኗ፣ በአህጉሪቱ የሚቀረጹ የሕፃናት መብትና ደህንነት ፖሊሲዎች መነሻ መሆኗ፣ አዲስ አበባ ጉባኤውን እንድታዘጋጅ መመረጧ ዲፕሎማሲያዊ ክብደት እንዳገኘች የተለያዩ ምንጮች ያስረዳሉ።
በአስማረ መኮንን