AMN – ሐምሌ 30/2018 ዓ.ም

በባሕር ዳር ከተማ የተከናወኑ ግዙፍ የመሠረተ ልማት፣ የቱሪዝም እና አገልግሎት የማዘመን ሥራዎች የከተማዋን ሁለንተናዊ አቅም ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግሩ መሆናቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የባሕር ዳር ደጃዝማች በላይ ዘለቀ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አዲሱ ተርሚናልን በመረቁበት ወቅት መልዕክት አስተላልፈዋል።

ከተማዋ ከመቶ ዓመታት በላይ ከመሀል ሀገር እስከ ሰሜን ኢትዮጵያ ለነበረው የንግድ እንቅስቃሴ ቁልፍ ድልድይ ሆና ማገልገሏን ያወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፤ አሁን ላይ ይህን ታሪካዊ ዳራ ከመልካም የልማት ጅምሮች ጋር በማቀናጀት አዲስ ምዕራፍ ላይ እንደምትገኝ ተናግረዋል።

በባሕር ዳር እና ጎርጎራ መካከል ያለውን የትራንስፖርት ትስስር በማሻሻል፣ እንደ “ጣና ነሽ” ያሉ ግዙፍ መርከቦችን በመጠቀም ታሪካዊ ደሴቶችንና ቅርሶችን የሚጎበኙ ሰዎችን ቁጥር ለማሳደግ የሚያስችሉ ሥራዎች መከናወናቸውን ጠቅሰዋል።

በአቪዬሽን ዘርፍ ደግሞ ከቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት ቀጥሎ በሀገሪቱ ሁለተኛው ትልቅ የሆነው አዲስ ተርሚናል በባሕር ዳር ተገንብቶ ለአገልግሎት መብቃቱ ለከተማዋ፣ ለክልሉ እና ለሀገር አቀፍ ኢኮኖሚ ትልቅ ገበያ አምጪ እንደሚሆን ተናግረዋል።
በተጨማሪም ከተማዋ በጥሩ ንድፍ ከተገነቡ የውስጥ ለውስጥ መንገዶች ባሻገር፣ በግዝፈቱ እና በጥራቱ ተወዳዳሪ የሌለውን ግዙፍ ድልድይ እና የኮሪደር ልማት ሥራዎችን በማከናወን ላይ እንደምትገኝ ገልጸዋል።

የኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ መጠናቀቁ እና በአሁኑ ወቅት እየተገነባ የሚገኘው ስታዲየም ሲጠናቀቅ ከተማዋን የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገር እንግዶች ማዕከል እንደሚያደርጋት ጠቁመዋል።
በፍትህ ዘርፍም በአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በተካሄደው ሪፎርም በመላው ክልል የሚደረጉ ችሎቶችን እና አቤቱታዎችን በኦንላይን መከታተል የሚያስችል የቴክኖሎጂ ዝርጋታ ተጠናቆ ሥራ መጀመሩን አድንቀዋል።

በሌላ በኩል፣ እነዚህን የተገነቡ ግዙፍ መሠረተ ልማቶች፣ የኮሪደር ሥራዎች እና የአረንጓዴ ልማቶችን የመጠበቅ እና የማደስ ሥራዎችን አጠናክሮ ለመቀጠል የከተማዋን የገቢ አቅም ማሳደግ ወሳኝ እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብራርተዋል።

በአሁኑ ወቅት ባሕር ዳር በሀገር አቀፍ ደረጃ በገቢ መጠን 7ኛ ደረጃ ላይ የምትገኝ በመሆኗ፣ ደረጃዋን የሚመጥን እና የከተማዋን እውነተኛ አቅም የሚያወጣ የገቢ አሰባሰብ ሥራ ሊሰራ እንደሚገባም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡
ለአካባቢው ነዋሪዎች፣ ለቱሪስቶች እና ለባለሀብቶች ምቹ አካባቢን በመፍጠር ከተማዋ ራሷን ችላ እንድታድግ የክልሉ መንግስት እና ነዋሪዎች ከከተማ አስተዳደሩ ጋር ተባብረው መስራት እንደሚገባቸውም አስገንዝበዋል።
በወርቅነህ አቢዮ