AMN- ጥቅምት 16/2019 ዓ.ም
በአዲስ አበባ እየተከናወኑ የሚገኙት የወንዝ ዳርቻዎችና የኮሪደር ልማት ፕሮጀክቶች መዲናዋን ውብ፣ ጽዱ እና ከብክለት ነጻ ከማድረግ ባለፈ፤ የሀገር ውስጥ አቅምን በመገንባት እና የኢኮኖሚ መነቃቃትን በመፍጠር ረገድ ለሌሎች ትላልቅ ከተሞች ትልቅ ተምሳሌት እየሆኑ ይገኛሉ።
እነዚህ ግዙፍ የኮሪደርና የወንዝ ዳርቻ ፕሮጀክቶች፤ አረንጓዴ ኮሪደሮችን፣ የስፖርትና የመዝናኛ ስፍራዎችን፣ የእግረኛ፣ የብስክሌትና ሰፋፊ የመኪና መንገዶችን እንዲሁም ዘመናዊ የንግድ ማዕከላትን አካተው ይዘዋል።
ቀደም ባሉት ጊዜያት መሰል ታላላቅ የመሠረተ ልማት ስራዎች የውጭ ሀገር ባለሙያዎችንና አማካሪዎችን እጅ የሚጠብቁ የነበሩ ቢሆንም፤ አሁን ላይ የእነዚህ አዳዲስ ፕሮጀክቶች የንድፍ እና ትግበራ ስራዎች ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ በሀገር ውስጥ መሐንዲሶች መከናወናቸው ትልቅ ስኬት ነው።
ይህም “በራሳችን አቅም አይሠራም” የሚለውን የተሳሳተ አመለካከት በመስበር የኢትዮጵያውያን ባለሙያዎችን የላቀ የመፈጸም አቅምና ብቃት በተግባር አሳይቷል።
በዚህም በኮንስትራክሽን፣ በኢንጂነሪንግ፣ በአርክቴክቸር፣ በመልክዓ-ምድር ውበትና በሎጂስቲክስና መሰል ዘርፎቸ የተሰማሩ የሀገር ውስጥ ተቋማት አቅማቸው እንዲጎለብትና በከፍተኛ ደረጃ እንዲነቃቃ አስችሏል።
ከእንጦጦ እስከ ፒኮክ እና ሩዋንዳ ድልድይ ድረስ ካለው 22 ነጥብ 7 ኪሎ ሜትር ፕሮጀክት ውስጥ፤ ከቀጨኔ በአምባሳደርና በኢሬቻ እስከ ባምቢስ የተዘረጋው 10 ኪሎ ሜትር ተመርቆ ለሕዝብ ክፍት ሆኗል።
በዚህም 351 ሄክታር መሬት በማልማት ከ300 ሺህ በላይ ሀገር በቀል ችግኞች ተተክለዋል።

በተከናወነው ሰፊ የመሰረተ ልማት ዝርጋታም 16 ኪሎ ሜትር የኮኔክቲቪቲ አስፋልት መንገድ፣ ከ1 ሺህ በላይ ተሽከርካሪዎችን የሚያስተናግዱ 22 ፓርኪንጎች፣ 8 የኤሌክትሪክ ቻርጂንግ ጣቢያዎች፣ 18 ኪሎ ሜትር የሳይክል መንገድ፣ 22 ኪሎ ሜትር የእግረኛ መንገድ፣ 5 ኪሎ ሜትር የመሮጫ ትራክ፣ 21 የልጆች መጫወቻዎች፣ 15 የስፖርት ሜዳዎች፣ 41 ድልድዮች እና 6 አነስተኛ ግድቦች ተገንብተዋል።
የአካባቢው ነዋሪዎችን የቀደመ ችግር ለመቅረፍ 6 ኪሎ ሜትር የንጹህ ውሃ መስመር እና 24 ኪሎ ሜትር የድሬኔጅና ስዌሬጅ መስመር ተዘርግቷል።
30 ካፌዎች፣ የመጻሕፍት ማንበቢያዎች እንዲሁም በእደ-ጥበብ ባለሙያዎች 108 ሱቆች በተዘጋጁበት ሞል ውስጥ በርካታ ወጣቶችና የእደ-ጥበብ ባለሙያዎች ተጠቃሚ መሆን ችለዋል።
በፕሮጀክቱ የግንባታ ሂደት ከ56 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል የተፈጠረ ሲሆን አሁንም በንግድ፣ በአገልግሎት፣ በመዝናኛና በአረንጓዴ ልማት እንክብካቤ ዘርፎች ለበርካታ ዜጎች የሥራና የገቢ ዕድሎች እየተፈጠሩ ነው።
በአዲስ አበባ እየተከናወኑ ያሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ሕዝብ፣ ባለሀብት እና የመንግሥት ተቋማት በቅንጅት ሲሰሩ የላቀ ውጤት ማምጣት እንደሚቻል አሳይተዋል፡፡
ከተማዋን ውብ ፣ ጽዱ እና ለነዋሪዎቿ ምቹ እያደረጉ የሚገኙ መሰረተ ልማቶችን ነዋሪዎች በባለቤትነት ስሜት በመጠበቅና በመንከባከብ ሊጠቀሙበት ይገባል፡፡
በትዝታ መንግስቱ